አገር አቀፍ የታክስ ንቅናቄ ዓርብ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የታክስ ንቅናቄ ዓርብ ይጀመራል
አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2011 አገር አቀፍ የታክስ ንቅናቄ የፊታችን ዓርብ ታህሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም የሚጀመር መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። ከታክስ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እና የሚደረጉ ህገ ወጥነትን ለመካላከል ሁሉም እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ ሚኒስቴሩ ገልጿል። የገቢዎች ሚኒስቴር "ግዴታዬን እወጣለው፣ መብቴን እጠይቃለው" በሚል መሪ ሀሳብ አገር አቀፍ የማህበሰረብ የታክስ ንቅናቄ የሚያካሂድ ሲሆን የፊታችን አርብ የንቅናቄ መክፈቻ ስነስርዓቱን በአፍሪካ ህብረት ያካሂዳል። የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ከታክስ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እና የሚደረጉ የህገ ወጥነትን ለመከላከል የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በአገሪቱ የታክስ ገቢ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፣ ሁሉም ህብረተሰብ የጀመረውን ህገ ወጦችን የማጋለጥ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል። አገር አቀፍ የታክስ ንቅናቄው በይፋ ሲጀመር ከአንድ ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳታፉ ሚኒስትሯ ገልጸዋል። የሚሰበሰበው አገራዊ ገቢ እየቀነሰ መጥቶ ከአገራዊ አጠቃላይ ምርት ያለው ጥምርታ 10 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ለዚህም በአገሪቱ ስር የሰደዱ ችግሮች የግብር ማሰባሰቡና የታክስ ፖሊሲ አውጪው ድክመት፣ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ፣ የተደራጀ ሌብነት፣ በታክስ ስወራ ማጭበርበርና በኮንትሮባንድ ወንጀሎች ዙሪያ የሚታዩ ጥፋቶች በሚፈለገው መልኩ ግብር ለመሰብሰብ አዳጋች ሆኗል። በንግዱ ማህበረሰብ ትክክለኛ ግብርን አሳውቆ መክፈል ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍም ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እና ልዩ ልዩ የገቢ አሰባሰብ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ይተገበራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በንቅናቄው የንግዱ ማህበረሰብ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ከፌዴራልና ከክልሎች የተወጣጡ ሰዎች ተሳተፊ ይሆናሉ። የሚሰበሰበውን ታክስ ለማሳደግ የሚያስችል፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ወር በፊት የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕላን ልማት ኮሚሽን፣ ብሔራዊ ባንክ የሚሳተፉበት አጠቃላይ ታክስን ሪፎርም ለማድርግ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ይገኛል። አጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በገቢ ማሰባሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ንቅናቄ ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን ንቅናቄው ለአንድ ዓመት የሚቆይ ነው። በንቅናቄው ላይ መልካም አፈጻጸም ያላቸው ግብር ከፋዮች እና ድርጅቶች እውቅናና ሽልማት ይሰጣል፣ በተመሳሳይ መልኩ በክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ ይካሄዳል ተብሏል።