በሐረር ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ ለማድረግ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች ይሮጣሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ ለማድረግ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች ይሮጣሉ
ሐረር ግንቦት 17/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 7ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመጪው እሁድ በሐረር ከተማ በሚካሄደው የሩጫ ውድድር ላይ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉ የክልሉ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ እስክንድር አብዱረሃማን ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት ሕብረተሰቡ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ ማጠናከር ዓላማው ባደረገው ታላቁ የሩጫ ውድድር 7 ሺህ 759 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። ከተወዳዳሪዎች የከናቲራ ሽያጭ የተገኘውን ከ775 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በሕዳሴ ግድብ አካውንት ገቢ መደረጉን ጠቁመው ተወዳዳሪዎቹም በአሁኑ ወቅት በፖስታ ቤት በኩል የመወዳደርያ ከናቲራቸውን በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በውድድሩም ሆነ በከናቲራ ግዥው የሴክተር መስሪያ ቤትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሠራተኞች፣ ማህበራት፣ የፍትህ አካላት፣ ወጣቶችና፣ ሴቶች፣ ህጻናትና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን አመልክተዋል። የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ያህያ ዘከርያ በበኩላቸው “ ስለ አባይ እሮጣለሁ ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የሰባት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር አዋቂዎች፣ ሕጻናትና አካል ጉዳተኞን ጨምሮ በስምንት ምድብ ውድድር እንደሚካሄድ ተናግረዋል። መነሻውን ሐረር በር መድረሻውን አስተዳደር ጽህፈት ቤት በሚያደርገው የሩጫ ውድድር ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። አቶ እስክንድር እንዳሉት፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ቀን ጀምሮ በክልሉ ከሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ አነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት፣ ከአርሶ አደሮች፣ ከነዋሪዎችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ከክልሉ ተሰብስቦ ገቢ ተደርጓል።