ቀጥታ፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አገር አቀፍ የወጣቶች የሰላምና የንቅናቄ ኮንፍረንስ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2011 በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ የወጣቶች የሰላምና የንቅናቄ ኮንፍረንስ ሊካሄድ መሆኑን የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ። ኮንፍረንሱ ከ1 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት ሲሆን ከሁሉም ክልሎች ከተለያዩ አደረጃጀቶች፣ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከአርሶ አደሮችና በማንኛውም ዘርፍ አረአያ ከሆኑ ወጣቶች የተውጣጡ መሆናቸውም ታውቋል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ በመግለጫው ላይ እንዳሉት፤ ኮንፍረንሱ "ወጣቶች ለአገር ለውጥና ሰላም" በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ነው። የኮንፍረንሱ አላማ ወጣቱ አሁን ለመጣው ለውጥ ዋና ተዋናይ እና ባለቤት እንደመሆኑ ሁሉ የሃገርን ሰላምና ልማትን በማስቀጠል ረገድ በቀጣይ እንዲሳተፍና የመጣው ለውጥ ፍሬ እንዲያፈራ የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሆኑንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታረቀኝ አብዱልጀባር በበኩሉ ወጣቱ ላለፉት አመታትና አሁንም ድረስ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች እንዲመለሱ ቅድሚያ የአገር ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብሏል። በተለይም የአገርን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማጎልበት የወጣቱ ድርሻ ትልቅ መሆኑንና በኮንፍረንሱ የሚሳተፉ አካላት ሃሳባቸውን በነፃነት በማንሳት በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አመለካከት የሚፈጠርበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርም ተናግሯል። ወጣቶቹ ከስልጠናው በኋላ ወደመጡበት ክልል ሲመለሱም ከዚህ ይዘውት የሄዱትን እውቀትና ግንዛቤ በማካፈል የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁሟል። ኮንፍረንሱ ታህሳስ 11 በአዲስ አበባ በብሄራዊ ስብሰባ ማዕከል ለአንድ ቀን የሚካሄድ ሲሆን ይህ አይነቱ የንቅናቄ ኮንፍረንስ በቀጣይ በየደረጃውና በየክልሉ የሚካሄድ መሆኑ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም