ቀጥታ፡

የአገራት አምባሳደሮችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በቀድሞው ፕሬዚዳንት ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን እየገለፁ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2011 በኢትዮጵያ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ ላይ ናቸው። አምባሳደሮቹ በአዲስ አበባ በተለምዶ የድሮው ጦር ኃይሎች በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት በመገኘት ነው ሀዘናቸውን እየገለፁ የሚገኙት። በተለያዩ አገራት ተመድበው የሚሰሩ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችም በተመሳሳይ ሀዘናቸውን ገልፀዋል። በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የቻይና፣ ከፖርቹጋል፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ አሜሪካ፣ ራሽያ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ህንድ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኒጀር፣ ፊንላንድና ፍልስጤምን ጨምሮ በርካታ አምባሳደሮች በቀድሞው ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት በተዘጋጀው የሀዘን መግለፃ መዝገብ ላይ ሀዘናቸውን የተመለከተ መልዕክት አስፍረዋል። አምባሳደሮቹ በዚሁ መልዕክታቸው ፕሬዚዳንቱ ከወጣትነት ጀምሮ ህዝባቸውንና አገራቸውን በማገልገል የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የተወጡ፤ ለአገራቸውና ህዝባቸው ፍፁም ተቆርቋሪ  መሪ እንደነበሩ አመልክተዋል። አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከመንግስታዊ ኃላፊነታቸው ባሻገር በተለያዩ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ማህበራዊ የበጎ ተግባራቸውም በስፋት የሚታወቁ እንደነበሩ አምባሳደሮቹ ጠቅሰዋል። በተለይም በኢትዮጵያ አደጋ ላይ የወደቀውን የደን መመናመን ለመከላከልና የፖሊዮ በሽታን ለማጥፋት በተደረጉ የተለያዩ ጥረቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ያበረከቱትን አስተዋፅኦም አምባሳደሮቹ አስታውሰዋል። በአጠቃላይ ለአገራዊ ልማት፣ ለእናቶች፣ ለህጻናትና ለወጣቶች ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ መጎልበት በርካታ በጎ ተግባራት አንደነበራቸውም ተመለክቷል። በመኖሪያ ቤታቸው የተገኘችው የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገረቻቸው አንዳንድ አምባሳደሮች ፕሬዝዳንት ግርማ አቅማቸውንና አውቀታቸውን  ሳይሰስቱ ለአገር በጎ ተግባር ያበረከቱና ለትውልድ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ መሪ መሆናቸውን ነው የገለፁት። አምባሳደር ቶፊቅ  አብድላሂ   እንደተናገሩትአገራቸው ኢትዮጵያን  ተጥሮዋን በጣም የሚወዱ ፤የሚያከብሩ ፤አቅማቸውን የማይሰሰቱ ነበሩ፡፡ በህይወት እያሉም የአይነ ብሌናቸውን  ለአይን ባንክ ተሰጠቶ ማየት ችግር ላለባቸው እንዲውል ፍላጎታቸውንም አስታውሰውዋል፡፡ አምባሳደር በቀለ እንዳሻውበበኩላቸው “እርሳቸው ሁል ጌዜ ምክርም ሐሳብም ይሰጡ ነበር፤ በወጣትነት ዘመናችን በትህግስት እንድሰራና ሰራየዬን በትጋት እንድወጣ ያደረጉኝ ናቸው፤  ትልቅ ሰው ነበሩ  በጣም ሰው በወዳጅነታቸውና  በሐሰተሳሰባቸው የሚገርሙ ሰው ነበሩ” ነው ያሉት፡፡ “ታላቅ ሀዘን  ይሰማኛል እንዲሁም ፕሬዝዳንት ግርማ በኮልፌ ከሚገኘው የእኛ ኢምባሲ ጎረቤት ስለሆኑ በተደጋጋሚ ተገናኝተናል፤ ጓደኛሞችም ነበርን፤ በዚህም ክብር ይሰማኛል፤ የነበራቸውን ሞገስ አደንቃለሁ፤ ጥሩ ህይወት እንድንመራ ምሳሌ የሚሆኑ ሰው እንደሆኑም አስባለሁ” ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ቢንት ፎን ሎስዲርት ናቸው፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ሌሊት ነው። አቶ ግርማ ከ1994 እስከ 2006 ዓም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል። የቀድሞ ፕሬዚዳንት አስከሬን ነገ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ከጥዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ህዝባዊ ሽኝት ይደረግለታል። ከቀትር በኋላ 9 ሰዓት ላይም ሰርዓተ ቀብራቸው ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል መንግስት ባለስልጣናት፣ የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች፣ የከተማው ነዋሪ እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ይፈፀማል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ህልፈት ጋር በተያያዘ ነገ ብሄራዊ የሃዘን ቀን ሆኖ እንዲውል መታወጁ ይታወቃል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም