ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ - ኢዜአ አማርኛ
ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ
መቀለ ታህሳስ 9/2011 ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ። በመቀለ ከተማ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 4ኛው የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ጉባኤ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። በትግራይ ክልል በተካሄደው የሊጉ ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ ወይዘሮ መስከረም አበበ ደግሞ ምክትል ሆነው ተመርጠዋል። ከዚህ ቀደም ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የሊጉ ሊቀመንበር የነበሩ ሲሆን እሳቸው የሥራ ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ነው አዲስ ሊቀመንበር የተመረጠው። ሊጉ አጠቃላይ 115 አባላት ያሉት ሲሆን በአሁኑ ጉባኤ ከተገኙት 96 አባላት ተገኝተዋል። የሊጉ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) እንዲሁም ምክትል ሊቀመንበሯ ወይዘሮ መስከረም አበበ ደግሞ ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ነው። ከምርጫው በኋላ ንግግር ያደረጉት አዲሷ ተመራጭ ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ ለሰላም መስፈን፣ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ለአገር አንድነት እና ለህዝቦች መቀራረብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ቀጣዩን የሊጉ ጉባኤ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እንዲያዘጋጅ ተወስኗል።