ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የሚታየውን የበጀት ጉድለት በማስቀረት ለልማት ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

ጋምቤላ ታህሳስ 9/2011 በጋምቤላ ክልል በበጀት አጠቃቀምና በገቢ አሰባሰብ የሚታዩ ችግሮችን በማስቀረት ለልማት ሥራዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ። በክልሉ በበጀት አጠቃቀምና በገቢ አሰባሰብ ችግሮች ዙሪያ ያተኮረ የፓናል ውይይት ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ በየዓመቱ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች በበጀት ጉድለት፣ በአጠቃቀምና በገቢ አሰባሰብ ችግሮች ምክንያት ነው። ችገሮቹ ሕዝቡ የሚነያሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ አስቸጋሪ እንዳደረጉትም ተናግረዋል። በተለይም በወረዳዎች የሚታዩ ችግሮች በልማት ሥራዎች አፈጻጸም ላይ  ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል። በመሆኑም የበጀት አጠቃቀምንና የገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን በማሻሻል በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዘበዋል። የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቢተር ሆው በበኩላቸው በክልሉ የሚታየው የገንዝብ ብክነትና የገቢ አሰባሰብ ችግሮች ካልተፈቱ ክልሉ የበጀት ቀውስ  ሊያጋጥመው ይችላል ብለዋል። ስለሆነም በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ችግሮቹን ለመፍታት እንዲሰሩ አሳስበዋል። በክልሉ ለሚታየው የበጀት ጉድለት ዋነኛ ምክንያቶች የገቢ አሰባሰብ፣ የበጀት የአጠቀቀም፣ ያልተገባ የሰው ኃይል ቅጥርና የደመወዝ ክፍያ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በውይይቱ  ጥናታዊ ጹሁፍ ያቀረቡት አቶ አበበ ጤናው ናቸው። በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ክልሉ የ273 ሚሊዮን ብር የበጀት ጉድለት አጋጥሞ እንደነበርና በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 230 ሚሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ሊያጋጥም እንደሚችል አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡቦንግ ኘል በሰጡት አስተያየት በተለይም ያልተገባ የሰው ኃይል ምደባና ቅጥር በሚፈጽሙ ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል። በተጨማሪ ያልተገቡ ወጪዎችን በመፈጸም የሕዝብ ሀብት የሚያባክኑ ተቋማትና ግለሰቦችን ላይ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ገቢ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት የተሰጠውን ተልኮ በአግባቡ እንዲወጣ ሁኔታዎች ተስተካክለውለት ኃላፊነቱን  አለመወጣቱ የተጠያቂነት የአሰራር ሥርዓት ያለመኖር ችግር ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ኦኬሎ ኡማን ናቸው። በጋምቤላ ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት ላይ ከፍተኛ የአመራር አካላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም