ቀጥታ፡

ከቡሬ አጋምሳ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በእቅዱ መሰረት አለመከናወኑ እንዳሳሰባቸው የፕሮጀክቱ ሰራተኞች ተናገሩ

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2011  ከቡሬ አጋምሳ በ6 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የአስፓልት መንገድ ግንባታ በእቅዱ መሰረት መከናወን አለመቻሉ እንዳሳሰባቸው የፕሮጀክቱ ሰራተኞች ተናገሩ፡፡ ተቋራጩ ተገቢውን ደመወዝ ባለመክፈሉ ለከፋ ችግር አጋልጦናል ሲሉም  ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አይ ቲ ኤን ኤል ኤልሳሜክስ በተባለ ተቋራጭ ከለቀምት ቡሬ በመገንባት ላይ የነበሩት ሁለት የመንገድ ስራ ኮንትራቶችን ውል ሊያቋረጥ መሆኑን አስታቋል፡፡ የነቀምት ቡሬ 257 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አስፓልት መንገድ ስራ ግንባታ የተጀመረው በፈረንጆቹ 2016 ነው፡፡ በመርሃ ግብሩ መሰረት የመንገዱ ግንባታ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን የጥገና እና የማስተዳደር ስራዎች ደግሞ የአምስት ዓመታት ጊዜ ተይዞላቸዋል፡፡ ለግንባታ የሚሆነው ወጪ በአለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡ ለስራው አመቺነት ሲባልም ግንባታው ለሶስት ተቋራጮች እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ኮንትራት አንድና ኮንትራት ሶስትን ITNL­_ELSAMEX የተባለው የህንድና ስፔን ጥምር ተቋራጮች ድርጅት ፣ኮንትራት ሁለትን ደግሞ ጂ ኤም ሲ የተባለው የህንድ ስራ ተቋራጭ ውል ወስደው ወደ ግንባታ ገብተዋል፡፡ በእቅዱ መሰረት አጠቃላይ ግንባታው ስራ በተያዘው የፈረንጆች ወር ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከቡሬ አጋምሳ በሚገነባውና 84 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው ኮንትራት ሶስት ፕሮጀክት የሚሰሩ ሰራተኞች የአስፓልት መንገድ ግንባታውን ውል ወስዶ ይሰራ የነበረው ITNL ­_ ELSAMEX የተባለ የመንገድ ስራ ተቋራጭ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ማከናወን አለመቻሉ አሳስቦናል ይላሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ በሰጡት አስተያየት ፡፡ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው ከለቀምት ቆፍቆፌ 86 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ፕሮጀክት አንድ አፈጻጸሙ 10 በመቶው ላይ ይገኛል፡፡ ከቆፍቆፌ አጋምሳ የ87 ኪሎሜትር መንገድ ግንባታ 12 በመቶው ብቻ ተከናውኗል፡፡ ቅሬታ አቅራቢ ሰራተኞቹ የሚገኙበት የአጋምሳ ቡሬ 84 ኪሎሜትር ፕሮጀክት 3 መንገድ ግንባታ ደግሞ ከ10 በመቶው በላይ መሻገር አልቻለም፡፡ የባለስልጣኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ መንገዱ በታሰበው ደረጃ አለመከናወኑን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለግንባታው መጓተት ምክንያት ናቸው የተባሉት ችግሮች በተፈቱበት ወቅትም ቢሆን ተቋራጩ አሰራሩን ፈትሾ ማስተካከል አለመቻሉ ግንባታው ከተገቢው በላይ እንዲጓተት አድርጎታል ይላሉ አቶ ሳምሶን፡፡ ድርጅቱ በውሉ መሰረት መንገዱን መገንባት የሚችልበት ቁመና ላይ አይገኝም ፡፡ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱን የመፈጸም ብቃትም የለውም የሚል አስተያየት ከሰራተኞቹ ይነሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባስልጣን ግን ድርጅቱ የልምድ ችግር እንደሌለበት ነው የሚናገረው፡፡ ፕሮጀክቱ ያሰማራቸው የስራ መሳሪያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆንና በተደጋጋሚ የሚበላሹ መሆናቸው ለስራው መጓተት ምክንያት መሆናቸው በሰራተኞቹ የተነሳ ሌላው አስተያየት ነው፡፡   ድርጅቱ በእነዚህና በውስጡ ባለው የአስተዳደር ችግር ምክንያት አልፎ አልፎ ይሰራ የነበረውን የመንገዱን ግንባታ ከነሐሴ ወር 2010 ዓ/ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ማቋረጡን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። በድርጅቱ ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞችም ከ2 እስከ 6 ወር የሚደርስ ደመወዝ አለመከፈላቸውን ጠቁመው፣ ችግሩ እንዲፈታ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም አለመፈታቱንና ይባስ ብሎም የድርጅቱ ኃላፊና አማካሪ ከስራ ቦታ መሰወራቸውን ገፀዋል። ሰራተኞቹ የመንገድ ግንባታው እየገጠመው ያለው ችግር እንዲፈታ ለሚመለከተው አካል ሁሉ ብናመለክትም የሚሰማን አካል ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ያስረዳሉ፡፡ የመንገዱ ግንባታ በቀጥታ የሚመለከተው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ቦታው ድረስ በመገኘት የሚያደርገው ክትትል ያነሰ መሆኑ ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ከሰራተኞች ደመወዝ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አይመለከትም ፤የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁን መሰረት በማድረግ በህግ መጠየቅ አለባቸው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል - አቶ ሳምሶን፡፡  ባለስልጣኑ ክትትልና ድጋፍ  በሚገባ አያደርግም የሚለውን አስተያየት አይቀበሉትም፡፡ ከቡሬ ነቀምት በሶስት ተቋራጮች በመካሄድ ላይ ያለው መንገድ ግንባታ እየተገባደደ ባለው በ2018 የሚጠናቀቅ ቢሆንም የሶስቱም ኮንትራቶች አጠቃላይ አፈጻጸማቸው አሁን ላይ ከአስራ አንድ በመቶው መሻገር ያልቻለ ነው፡፡ አቶ ሳምሶን እንዳሉት ባለስልጣኑ የፕሮጀክት ሁለት አፈጻጸም የተሻለ በመሆኑ ግንባታው እንዲቀጥል የደረጋል፡፡ ፕሮጀክት አንድንና ሶስትን ግን ተቋራጩ በተደጋጋሚ በሚሰጠው አስተያየት እና ማስጠንቀቂያ መሰረት ማስተካል ባመቻሉ ውሉን በማቋረጥ ለሌላ ተቋራጭ ለመስጠት በሂደት ላይ ነን ይላሉ፡፡ ኤዜአ በጉዳዩ ላይ የITNL ­_ ELSAMEX አስተያየት ለማካተት በስልክና በአካል ሙከራ ቢያደርግም የድርጅቱን ኃላፊዎች ማግኘት አልቻለም፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም