የኢትዮጵያ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የቮሊቦል ሻምፒዮና በቀጣዩ ወር ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የቮሊቦል ሻምፒዮና በቀጣዩ ወር ይካሄዳል
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የቮሊቦል ሻምፒዮና በቀጣዩ ወር ከሰኔ 14 እስከ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታወቀ። በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ180 በላይ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። በዚህም መሰረት የትግራይ፣ የቤኒሻንጉልና የደቡብ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳር በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በደብዳቤ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ የሶማሌ ክልል በበጀት እጥረት ምክንያት በውድድሩ ላይ እንደማይሳተፍ ማሳወቁን ተናግረዋል። የተቀሩት ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ቃል መግባታቸውንና የተሳታፊዎች ምዝገባ እስከሚጠናቀቅበት ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም መወዳደራቸውን በደብዳቤ ያሳውቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። ሻምፒዮናው ተተኪ የቮሊቦል ስፖርተኞችን ለማፍራትና ለኢትዮጵያ የወንዶችና የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች ተጫዋቾችን ለመመልመል እንደሚያስችል ጠቅሰዋል። በሻምፒዮናው አሸናፊ ለሚሆኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት እንደሚሰጣቸውና በቀጣይ ዓመት በሁለቱም ጾታዎች በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖችን የማሳተፍ እድል እንደሚሰጣቸው አቶ ተክሉ አስረድተዋል። የቮሊቦል ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ የገባው አገሪቱ ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀምር በአብዛኛው በውጭ መምህራን ስለነበር መምህራኑ ስፖርቱንም እንዳስጀመሩት በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ያሳያሉ። የስፖርቱ መዘውተር በ1957ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን እንዲመሰረት አስችሏል። በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1980ዎቹ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ ያሳየው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ስፖርት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ቀድሞ ኃያልነቱ ለመመለስ በወንድም በሴትም የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ማካሄድን ጨምሮ የተለያዩ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።