ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚው ለማድረስ እየተሰራ ነው

አዳማ ታህሳስ 8/2011 የአየር ንብርት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ የተመረጡ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚው ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ። በኮሚሽኑ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ወይዘሮ የአምላክስራ ታመነ እንዳሉት ችግሩን በራስ አቅም ለመቋቋም እየተሰራ ያለው ከከፍተኛ ትምህርት፣ የምርምር ተቋማትና በዘርፉ የፈጠራ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ነው፡፡ "28 የተመረጡ በራስ አቅም በሀገር ውስጥ የተፈበረኩ አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን የመለየትና በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል" ብለዋል። ባለፈው የበጀት ዓመት በተካሄደው ጥናት በግብርና፣ ኢነርጂ ፣ትራንስፖርት፣ኢንዱስትሪና ደረቅ ቆሻሻ ብቻ ሀገሪቱ 150 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በካይ ጋስ ወደ አካባቢ አየር መልቀቁን እንደተረጋገጠ አመልክተዋል። "ወደ አካባቢ አየር ከተለቀቀው ሙቀት አማቂ ጋዞች ውስጥ 50 በመቶ ድርሻ የሚይዘው ግብርና ነው "ያሉት ዳይሬክተሯ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግም የአፈር ለምነትን መጠበቅ የሚያስችሉ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ልማት እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በግብርና መስክ ብቻ የሚለቀቀውን 75 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሙቀት አማቅ በካይ ጋስ ለመቀነስ 12 የተመረጡ ቴክኖሎጂዎች ተለይተው ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ተክኖሎጂዎቹ በተለይም የኬሚካል ማዳበሪያዎችን የሚተኩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት መጠቀም የሚያስችሉና ጥምር ግብርናን  ለመተግበር የሚያግዙ ናቸው። የደን ውድመትን  ለመቀነስ የሚያስችሉ   ስድስት  የተመረጡ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ ለማዋል ባዮ ፊውልና ሶላር የተባሉ ኢነርጂዎች  በውህደት መጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ በባህርዳር ዩኒቨርስቲ  መፈብረኩን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። "ቴክኖሎጂ ዘመናዊና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር ጊዜና ወጪን የሚቆጥብ ነው" ብለዋል። በተያዘው የበጀት ዓመት በሙከራ ደረጃ በስድስት የሀገሪቱ ክልሎችና በ12 ወረዳዎች 55ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአርንጓዴ ቴክኖሎጂ ትግበራ መጀመሩንም አመልክተዋል። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ  መምህር ብስራት ይልማ በበኩላቸው በምርምር የተገኘው ቴክኖሎጂ ባዮ ፊውልና ሶላር ኢነርጂን በአንድነት አቀናጅተው አገልግሎት ላይ ለማዋል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። የህብረተሰቡን ባህላዊ የምግብ ዝግጅትና የቤት ውስጥ አገልግሎትን ግምት ውስጥ ያስገባ ጭምር መሆኑን ጠቅሰው አንድ ማብሳያ ምድጃ በአንድ ጊዜ  ሶስት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። ከፋብሪካዎች የሚወጡ ተረፈ ምርቶችና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂ መፍጠራቸውን የተናገሩት ደግሞ በትግራይ ክልል የሸበሌ ዞን ኢንዱስትሪ ማዕከል የፍሳሽ አወጋገድ ባለሙያ አቶ ሙሌን ሀጎስ  ናቸው። በተለይም ከቆዳ ፋብሪካዎች የሚወጡትን ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎችን ለማስወገድና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደያግዝ ጠቁመዋል፡፡ ከግብርና፣ኢነርጅ፣ትራንስፖርት፣ኢንዱስትሪና ደረቅ ቆሻሻ የሚለቀቁ በካይ የካርበን ጋዝ ለመቀነስ በዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች የተፈበረኩ አረንጓዴ  ቴክኖሎጂዎችን ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል። በመድረኩ ከዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት የተወጣጡ የፈጠራ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከፌዴራልና ከክልል የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም