አቶ አወል አርባ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

153
ሰመራ ታህሳስ 8/2011 የአፋር ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎችን ሹመቶችን አጽድቋል። በዚህም መሠረት አቶ አወል አርባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነዋል። አቶ ኡስማን መሐመድ ሁመዳ ምክትል ርዕስ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል። እንዲሁም ወይዘሮ አሚና ሴኮ የክልሉ ምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ  ሲሆኑ፤ወይዘሮ ሐዋ ከሎይታ ምክትል አፈ ጉባዔ አድርጎ ሾሟል። ምክር ቤቱ በርዕሰ መስተዳድሩ የቀረቡለትን የክልሉን ካቢኔ አባላትና የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች ሹመትም  አጽድቋል። አቶ አወል በዚሁ ጊዜ በአገሪቱ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለመተግበር የክልሉ መንግሥትና መሪ ፓርቲው የአፋር  ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አብዴፓ)ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ፓርቲው በቅርቡ ባደረገው ጉባዔ ነባር አመራሮችን በክብር በመሸኘት የተሻለ የትምህርት ዝግጅትና የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት የተላበሱ  ወጣቶችን ወደ አመራርነት ማምጣቱንም ተናግረዋል። ምክር ቤቱ  በክልሉ የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት ከአገራዊ የሪፎርም ሥራዎች ጋር ለማጣጣም ያዘጋጀው ማሻሻያ ዓዋጅ በማጽደቅ ጉባዔውን አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም