ቀጥታ፡

የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ወላጆች በትጋት እንዲሰሩ የሰላም አምባሳደሮች ጠየቁ

ጋምቤላ ታህሳስ 8/2011 የጋምቤላ ክልልን ሰላም ለማስጠበቅና ለማጠናከር ወላጆች በትጋት እንዲሰሩ የሴት የሰላም አምባሳደሮች ጠየቁ። ሴት የሰላም አምባሳደር ቡድን በጋምቤላ ከተማ ከእናቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በሰላም ዙሪያ ተወያይቷል። የቡድኑ አባላት በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ወላጆች በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም የሰላምን ጠቀሜታ እንዲያስተምሩና እንዲሰብኩ ጠይቀዋል። የቡድኑ መሪ ወይዘሮ ገነት አሰፋ እንዳሉት ሰላም ለሁሉም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መሠረት መሆኑን ገልጸው፣የክልሉን ሰላም  ለማስጠበቅ በተለይም እናቶች ማህበረሰቡን ማስተማርና መምከር እንዳለባቸው ተናግረዋል። በየትኛውም ሁኔታ በሰላም እጦት ተጎጂ የሚሆኑት እናቶች በመሆናቸው ሰላምን መስበክና ማስተማር አለባቸው ያሉት ደግሞ ሌላዋ የቡድኑ አባል ወይዘሮ አብሽሮ ሙሐመድ ናቸው። በመሆኑም ''እኛ እናቶች ልጆቻችን፣ ባሎቻችን፣ ወንድሞቻችንና አባቶችን በሰላም ወጥተው እንዲገቡ እንፈልጋለን፤ ስለዚህ አባቶችና እናቶች ለሰላም ትልቅ ዋጋ መስጠት አለባችሁ'' ብለዋል። ሌላዋ የቡድኑ አባል ወይዘሮ አበባ ተገኝ በበኩላቸው የክልሉን ሰላም በማስጠበቅና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እናቶች ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጠንክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኃይለማሪም ተክለማሪያም በሰጡት አስተያየት የስላም አምባሳደር እናቶችን አርአያነት በመያዝ ለሰላም ለመሥራት ቃል ገብተዋል።እስከ ገጠር ቀበሌዎች ድረስ ዘልቀው በመግባት ኃላፊነቴን እወጣለሁ ብለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የሕዝቡ አንድነት እንዲጠናከር እንደምትሰራ የተናገሩት ደግሞ ተወካይዋ አባ ቲቶ አዳነ ናቸው። ''እናቶች ከዚህ ድረስ በመምጣት በክልሉ ያለው ሰላም እንዲጠናከር የነገራችሁን ነገር ልባችን ነክቶናል። የሰጣችሁን የሰላም ሥራ ኃላፊነት ለመወጣት በአግባቡ ጥረት እናደርጋለን '' ሲሉም ተናግረዋል። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አርያት ኡጁሉ በበኩላቸው በእናቶች ልጆቻውን ሰለሰላም ማስተማርና መምከር እንዳለባቸው ገልጸዋል። ከዘጠኝ ክልሎችና ከሁለት ከተሞች አስተዳደሮች የተውጣጡት ሴት የሰላም አምባሳደሮች ከኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ቃል ማስገባት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል። የሴት ሰላም አምባሳደሮች ቡድን በሁሉም ክልሎች ለ25 ቀናት ጉብኝት አድርጓል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም