ቀጥታ፡

ወላይታ ድቻ ደቡብ ፖሊስን አሸነፈ

ሶዶ ታህሳስ 8/2011 በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም በተካሄደው ስድሰተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ድቻ ደቡብ ፖሊስን አንድ ለባዶ አሸነፈ፡፡ የፌዴራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ የመሩት የሁለቱ ቡድኖች የትናንቱ ጨዋታ በሰላማዊ መልኩ ተጠናቋል፡፡ የወላይታ ድቻ ቡድን አሸናፊ ያደረገቻቸዉን ግብ ያስቆጠረው በ48ኛው ደቂቃ ላይ በሶስት ቁጥሩ በአንዱዓለም ንጉሴ አቤጋ አማካይነት ነው፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኳስ በማደራጀት፤በመቀባበልና የመሃል የሜዳ ክፍል ብልጫ በመውሰድ ባለሜዳው የወላይታ ድቻ ቡድን የተሻለ ሆኖ አምሽቷል፡፡ በግብ ሙከራ ረገድ በተጨማሪ ሰዓት ስምንት ቁጥሩ አብድል ሰመድ መሃመድ የተጋጣሚው ግብ ጠባቂ በወጣበት ሞክሮ የሳታት ኳስ ደጋፊውን ያስቆጨች ነበረች፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ተጋጣሚው የደቡብ ፖሊስ በረጅሙ ኳስ በመወርወር፣ በመከላከልና አጥቅቶ በመጫወቱ የተጋጣሚውን ተከላካይ ክፍል በማስጨነቅና ወደ  ግብ ክልሉ ቶሎ ቶሎ በመድረስና ሙከራዎችን በማድረግ የተሻለ ነበር፡፡ ሆኖም ወደግብነት የሚቀይር ጠፍቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ሁለተኛዉ የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በዚሁ አጋጣሚ ነው የድቻው ሶስት ቁጥር አንዱዓለም ንጉሴ  ወይም አቤጋ ከቀኝ በኩል የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ሊያስቆጥር የቻለው፡፡ ከዚህ ግብ በኋላ የረባና ተጋጣሚውን ሊያስጨንቅ የሚችል ሙከራንም ሆነ ዕድል አልፈጠረም ድቻ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ፈጣን የኳስ ፍሰት የቀጠለ ሲሆን የደቡብ ፖሊስ የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠርና ባለሜዳውን በማስጨነቅ የተሻለ ሲሆን ድቻ ደግሞ ያገኘውን አጋጣሚ አስጠብቆ ለመውጣት ሲታትር ነበር፡፡ ተቀይሮ ከገባው 14 ቁጥር ለባሹ ከአንጋፋው ተጫዋች ከሙሉዓለም ረጋሳ በ86ኛ ደቂቃ ላይ ያሻገራትን 22 ቁጥሩ ብሩክ ኤልያስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመለጠው ኳስ ምናልባትም በደቡብ ፖሊስ በኩል አቻ ሊታደርጋቸው ትችል ነበር ማለት ያስችላል፡፡ የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ የተሻለዝግጅትና የማሽነፍ ፍላጎት ቢኖረንም እንደባለሜዳ ሸፍኖና አጥቅቶ አለመጫወታቸዉን ገልጾ በዉጤቱ መደሰታቸዉን ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ካሰቡት ልክ ተጋጣሚያቸዉ ተጭኖ መጫወቱ ድርሻ እንዳለዉ የገለጹት አሰልጣኝ ዘነበ በቀጣይ በተለይ ከማጥቃትና የግብ ዕድል ከመፍጠር ረገድ ያሉብንን ክፍተቶች ላይ እንሰራለን" ብሏል፡፡ የደቡብ ፖሊስ ቡድን ዋና አሰልጣን ዘላለም ሽፈራው በጨዋታው ላይ ካሳዩት ጥንካሬና ከፈጠሩት የግብ ዕድል አንጻር ሽንፈቱ እንደማይገባቸው ተናግረው ተጋጣሚያቸውም የግብ እድል አለመኖሩ እንጂ ተጋጣሚያቸውም እንዳልከበዳቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይም ቡድናቸው ግብ ከማስቆጠርና ከመናበብ አንጻር የሚስተዋልበት ክፍተት ላይ ከፍተኛ ስራ እንደሚጠብቃቸውና ቡድኑን በፕሪሚየር ሊግ ማቆየት ዋና ስራቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ብዛት ያላቸው  የክለቦቹ ደጋፊዎች በሜዳው በመገኘት ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ቡድናቸውን አበረታትተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም