ቀጥታ፡

የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በፕሬዚዳንት ግርማ ሞት የተሰማውን ኅዘን ገለጸ

ጋምቤላ ታህሳስ 7/2011 በቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሞት ከፍተኛ ኅዘን እንደተሰማው የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንደገለጸው ከወጣትነታቸው ጀምሮ በተለያዩ  የኃላፊነት ደረጃዎች አገሪቱን ያገለገሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከዚህች ዓለም በሞት በመለየታቸው አዝኗል። አገሪቱን ለ12 ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ መሪ እንደነበሩም አስታውሷል። ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን የተመረኮዘ አገልግሎት የሰጡ ታላቅ ሰው እንደነበሩ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። የክልሉ መንግሥት ለፕሬዚዳንት ግርማ  ቤተሰቦች ፣ወዳጆችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ተመኝቷል። ፕሬዚዳንት ግርማ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ሁለተኛው ርዕሰ ብሔር ሆነው አገልገለዋል። የቀድሞው ርዕሰ ብሔር በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ከትናነት በስቲያ ሌሊት ሕይወታቸው ያለፈው በ95 ዓመታቸው ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም