የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሞት ኅዘናቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሞት ኅዘናቸውን ገለጹ
ሐረር ታህሳስ 7/2011 በቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ህልፈተ ሕይወት ጥልቅ ኅዘን እንደተሰማቸው የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ ዛሬ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ እንዳመለከቱት ፕሬዚዳንት ግርማ በኢትዮጵያ የማይረሳና ዘመን ተሻጋሪ አገልግሎት የሰጡ ቅን አመራር ነበሩ። ''በሕይወት ላጣናቸው በአገሪቱ የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሞት የተሰማኝን ጥልቅ ኅዘን በክልሉ ሕዝብና በራሴ ስም እገልጻለሁ'' ብለዋል። በውትድርናና በተለያዩ ሙያዎች በመሰማራትና ለ12 ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት በቅንነትና በታማኝነት ያገለገሉ መሪ እንደነበሩም አስታውሰዋል። እስከ ሕይወት ህልፈታቸው ድረስ በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ገልጸዋል ። ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል። አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በርዕሰ ብሔርነት ያገለገሉት ከ1994 እስከ 2006 ድረስ ነበር።