በእጃችን ላለው ሰላም ቀጣይነት በአንድነት እንስራ---የሰላም አምባሳደር እናቶች - ኢዜአ አማርኛ
በእጃችን ላለው ሰላም ቀጣይነት በአንድነት እንስራ---የሰላም አምባሳደር እናቶች

ጋምቤላ ታህሳስ 6/2011 በእጃችን ላይ ስላለው ሰላም ዘላቂነት በአንድነት ተጠንክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ የሰላም አምባሳደር እናቶች ገለጹ። የሰላም አምባሳደሮቹ የልኡካን ቡድን አባላት ዛሬ ጋምቤላ ሲገቡ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በሁሉም አካባቢ በየደረጃው የሚገኝ አመራር ከህዝቡ ጋር በመሆን ለሰላም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በትጋት እንዲሰራም የልኡካን ቡድኑ አባላት ተናግረዋል። የዘላቂ ሰላም መታጣት በሃገር እድገትና በዜጎች የመኖር ተስፋ ላይ የራሱን የከፋ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ የቡድኑ ተወካይ ወይዘሮ ገነት አሰፋ ገልጸዋል። የቡድኑ ጉዞ ዓላማም የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅና አንድነትን ለማጠናከር እንደሆነና በተለይም ችግር ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከልን መሰረት ያደረገ ስራ ለመስራት መሆኑንም አመልክተዋል። ለዚህ ውጤታማነት የአመራሩ ሚና መጠናከር እንዳለበት የገለጹት ወይዘሮ ገነት በህብረተሰቡ ዘንድ ምንም አይነት ልዩነት አለመኖሩን መታዘባቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ የቡድኑ አባል ወይዘሮ ዮዲት ተስፋዬ በበኩላቸው የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰላምን ማስፈን ቀዳሚ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመፍታትና በህብረተሰቡ ዘንድ የቆየውን የአብሮነት ስሜት ይበልጥ ለማጠናከር በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሰላም ያለው በእያንዳንዳችን እጅ ናት ያሉት ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ክሮምስ ሊሮ “በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በተለይም እናቶች የሰላሙን አስፈላጊነት በመገንዘብ ልጆቻቸው ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳይገቡ መምከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ ሀገራት የውስጥ ሰላማቸውን ማስጠበቅ ባለመቻላቸው ከገቡበት የድህነት አዘቅት ለመውጣት እየተቸገሩ መሆኑን በመግለጽ “እኛም ከአሁኑ ለሰላምና አንድነት በትኩረት ልንሰራ ይገባል” ያሉት ደግሞ ሌላዋ አባል ወይዘሮ አሊፊያ የሱፍ ናቸው፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የክልሉን ሰላም ማስጠበቅ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግስት ሰላሙን በማስፈን ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ልኡካኑ እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። የሰላም አምባሳደሮቹ በዛሬው እለት የተገኙበትን የጋምቤላ ክልል ጨምሮ በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በመዘዋወር ተመሳሳይ የሰላም ውይይቶችን ከአመራሮች፣ከተማሪዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ማድረጋቸው ይታወሳል።