የድሬዳዋ ደወንሌ የኮንክሪት አስፋልት የክፍያ መንገድ ሥራ ሊጀመር ነው

134
ድሬደዋ ታህሳስ 6/2011 ከአምስት ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ ተገንብቶ የተጠናቀቀው የድሬዳዋ ደወንሌ የኮንክሪት አስፋልት የክፍያ መንገድ በሁለት ወራት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር የትራስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በመንገዱ አጠቃቀም ዙሪያ ሲቲ ዞንና ከድሬዳዋ አስተዳደር  አመራሮችና ነዋሪዎች ጋር ዛሬ ውይይት ተካሄዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት በትራስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ ከዲር እንዳሉት ከድሬዳዋ ደወንሌ የተዘረጋውን የ223 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ የሚሸፍን ነው፡፡ በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የተገነባውና ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘው  የአስፋልት መንገዱ በሁለት ወር ውስጥ በክፍያ አገልግሎት እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡ "መንገዱ የውጭና የገቢ ንግድ የሚያቀላጥፍ ይሆናል" ያሉትአቶ ሙስጠፋ  ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ የግብርናና የኢንዱስትሪ  ቁሳቁሶች ያለብልሽት በፍጥነት ለመጓጓዝ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ ከአዳማ-አዲስ አበባ የክፍያ መንገድ ቀጥሎ ሁለተኛው የክፍያ መንገድ ሆኖ የሚያገለግለው መስመሩ በቀን ዘጠኝ መቶ ተሸከርካሪዎች  እንደሚያስተናግድ አስረድተዋል፡፡ 85 በመቶ ወጪ ከቻይናው ኤግዚን ባንክ በተገኘ ብድር በቻይና ኮንስትራክሽን ድርጅት የተገነባው መንገድ ስራ ሲጀምር እስከ ሶስት መቶ ለሚሆኑ የሲቲ ዞንና የድሬዳዋ ነዋሪዎችን ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡ በሶማሌ ክልል የሲቲ ዞንና የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎችና አመራሮች አካላት ለመንገዱ ደህንነት ተቀናጅተው በመስራት  ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው "መንገዱ የህዝብ ጥያቄ ምላሽ ያስገኘና ለሀገሪቱ በተለይም ለምስራቁ ክፍል ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት ዕድገት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ያበረክታል "ብለዋል፡፡ መንገዱ በቅርቡ ከሚመረቀው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር የተገናኘ  መሆኑ  ድሬዳዋ የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን እየተከናወኑ ለሚገኙ ፈረጀ ብዙ ተግባራት መሳካት ሁነኛ ድርሻ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ መንገዱ ሙሉ በሙሉ የሚያቋርጠው በሶማሌ ክልል የሲቲ ዞን ንግድ ትራንስፖርትና መንገድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢድሪስ ጅብሪል መንገዱ ለአካባቢው አርብቶ አደር  ከእስሳት ሃብቱ ይበልጥ  እንዲጠቀም የሚስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "የዞኑም ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት እንዲጎለብት ያስችላል" ብለዋል፡፡ የመንገዱ ጥበት መሻሻልና በመንገዱ ሥራ ወቅት ለጉዳት የተዳረጉ የተፈጥሮ እፅዋቶች መልሰው እንዲያገግሙ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አሊ ሰመሬ በበኩላቸው በዞኑ  አስተማማኝ ሰላም መኖሩን አስታውሰው ለመንገዱ አስፈላጊውን ጥበቃና ከለላ በማድረግ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ የሲቲ ዞን የሀገር ሽማግሌ ሐጂ  ሙሴ ሜጋድ የመንገዱን ደህንነት በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቅሰው የመንገዱን ጠቀሜታ የተመለከተ የግንዛቤ መስጫ በየደረጃው ለሚገኘው ህብረተሰብ ማዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ "አደራ የምላችሁና የማሳስባችሁ የዞኑን ወጣት ቋሚ የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ነው" ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ ደወንሌ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ በሦስት ስፍራዎች ላይ የክፍያ ጣቢያ ይኖሩታል፡፡ የአዳማ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ደወንሌ እንዲሁም በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚጠናቀቁት የሞጆ -ሐዋሳ፣ የአዳማ  አዋሽ መንገዶች ጨምሮ በጥቅሉ በሀገሪቱ 643 ኪሎ ሜትር የክፍያ መንገዶች አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም