በዘውዲቱ መሸሻ የህጻናት መርጃ ማዕከል ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ንብረት ወደመ

53
አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2011 በአዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው ዘውዲቱ መሸሻ የህጻናት መርጃ ማዕከል ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ንብረት ወደመ። ትናንት ከሌሊቱ 9:00 ሠዓት ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ዛሬ ጠዋት 2፡00 ሠዓት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል። ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ቃጠሎው ያደረሰውን ጉዳት የተመለከተ ሲሆን ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲና ከአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የቃጠሎው መንስኤ ምን እንደሆነ ባይታወቅም የኤሌክትሪክ ምሰሶና ቆጣሪ ከማዕከሉ ወፍጮ ቤት ጋር ተገናኝቶ ነው የሚል ግምት መኖሩን የማዕከሉ የአስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ አበባየሁ ፍቃዱ ተናግረዋል። በቃጠሎው ሶስት የእህል ወፍጮዎች፣ ሶስት ፌዝ ቆጣሪ፣ መጋዘን፣ የሴቶች መኝታ ክፍል ከተለያዩ ቁሳቁሶችና ንብረቶች ጋር ወድመዋል። አቶ አበባየሁ እንዳሉት በእሳቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሟል፡፡ በቃጠሎ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩንም አክለዋል። ትናንት ሌሊት 9:00 ሠዓት የተነሳው ቃጠሎ የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ባለመድረሳቸው እስከ ንጋት መዝለቁንና በአካባቢው ማህበረሰብ ርብርብ ከጠዋቱ 2:00 ሠዓት ላይ መጥፋቱን ተናግረዋል። ኢዜአ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲና የአዲስ አበባ ፖሊስ የስራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ጥረት የሞባይል ስልኮቻቸውን ባለማንሳትና በመዝጋታቸው አልተሳካም። ዘውዲቱ መሸሻ የህጻናት መርጃ ማዕከል ከተመሰረተ 28 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 75 ህጻናትን በመደገፍ ላይ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም