ቀጥታ፡

ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2011 ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር ጨዋታውን ዛሬ ምሽት 2:00 ሰዓት ላይ ከግብጹ ክለብ አልአህሊ ጋር ያደርጋል። በ2019 የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመግባት የኢትዮጵያው ክለብ ጅማ አባ ጅፋር ዛሬ ምሽት 2:00 ሰዓት ላይ የግብጹን አልአህሊን ይገጥማል። ቻምፒየንስ ሊግ የአንደኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታውን ለማድረግ ቡድኑ 18 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ስፍራው አቅንቷል። ጅማ አባ ጅፋር ወደ አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ለማለፍ ከግብፁ አል አህሊ ጋር ምሽት 02:00 ሰዓት ላይ የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ ወሳኝ ይሆናል። ጨዋታው አሌክሳንድሪያ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ቦርግ አላ አርብ ስታድየም እንደሚደረግ ተገልጿል። የአምና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ጅማ አባጅፋር በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሊጉ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ጨምሮ በቅድመ ማጣሪያውም ጭምር ምንም ሽንፈት አላስተናገዱም። በአንጻሩ ተጋጣሚያቸው የግብፁ አል አህሊ ደግሞ በ2018ቱ የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ከተሸነፈ በኋላ በአዲሱ አሰልጣኙ መሐመድ ዩሱፍ እየተመራ ያደረጋቸውን ሦስት የሊግ ጨዋታዎችን ያሸነፈ ሲሆን አምስት ግብ አስቆጥሮ አንድም ግብ አልተቆጠረበትም። በቻምፒየንስ ሊጉ የመጀመርያ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር የጅቡቲውን ቴሌኮም 5 ለ 3 በሆነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል። ዛሬ ማምሻውን 2:00 ላይ በሚደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ጠንከር ያለ ፈተና እንደሚጠብቃቸው የሚገመት ሲሆን ጨዋታውን ቱኒዚያዊ ዳኛ የሚመሩት ይሆናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም