በፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ሃዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ይጠበቃል

62
አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሃዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። የሊጉ ስድስተኛ ሳምንት የጨዋታ መርሃ ግብሮች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሰረት አርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ስታዲየሞች የሚደረጉ ይሆናሉ። በዚህም ነገ አርብ ቀን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሜዳው ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ በ9:00 ሰዓት የሚደረግ ብቸኛው ጨዋታ ነው። ፋሲል ከተማ ከመከላከያ፣ ወላይታ ድቻ ከደቡብ ፖሊስ፣ ባህርዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ አደማ ከተማ ከመቐለ ሰብአ እንደርታ እንዲሁም ስሁል ሽረ ከሲዳማ ቡና ቅዳሜ በተመሳሳይ በ9:00 ሰዓት በክልል ከተሞች የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው። በዚሁ እለት መካሄድ የነበረበት የጅማ አባ ጅፋርና ደደቢት ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ባለበት የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር የተነሳ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሃዋሳ ከተማ እሁድ ከቀኑ በ10:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረግ ጨዋታ ነው። በዚህም ሃዋሳ ከተማ የሊጉ መሪነቱን የሚያጠናክርበት፤ በአንጻሩ አጀማመሩ ያላማረውና ከሶስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፍ የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ነጥብ ይዞ ለመውጣት የሚፋለሙ ይፋለማሉ። ይህም ጨዋታው ከወዲሁ በበርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል። ፕሪሚየር ሊጉን ሃዋሳ ከተማ በ10 ነጥብ እየመራ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናና ሲዳማ ቡና በእኩል 8 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ደቡብ ፖሊስ፣ ስሁል ሽረ፣ አዳማ ከተማ እና ደደቢት ደግሞ ከ13 እስከ 16ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ናቸው። የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ4 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ሲሆን ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና እስራኤል እሸቱ ከሃዋሳ ከተማ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው በእኩል ሶስት ጎሎች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም