ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊው ኮርፖሬሽን በጥምረት የሚከውነው የሩዋንዳ መስኖ ፕሮጀክት አፈጻጸም 90 በመቶ ደረሰ

አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2011 የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ከሌሎች ተቋማት ጋር በጥምረት የሚያካሂደው የሩዋንዳ ምዋንዛ መስኖ ፕሮጀክት አፈጻጸም 90 በመቶ መድረሱን ገለጸ። ፕሮጀክቱ የኮርፖሬሽኑን በቀጣናው የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራዎች፣ የግድብ፣ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድና ሌሎች ስራዎች ላይ የመሳተፍ ዕድል ያሰፋ መሆኑ ተነግሯል። የኮርፖሬሽኑ የውሃ መሰረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሁለት የውጭ አገር ኩባንያዎች ጋር በጥምረት የሚያካሂደው ከሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የምዋንዛ መስኖ ፕሮጀክት በ2011 ዓ.ም መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥንፉ ሙጬ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ የገባው ውል የፕሮጀክት አስተዳደሩን መምራት ነው። ''የእኛ የስራ ድርሻ ወይም አስተዋጽኦ የፕሮጀክቱን የግንባታ ስራ የመቆጣጠርና ግንባታ የማከናወን ተግባር ነው'' ብለዋል። ፕሮጀክቱ በግፊት ኃይል የሚሰራ መስኖ መሆኑንና ኮርፖሬሽኑ በዘርፉ ከተሰማሩ ሁለት የሩዋንዳ የግል ኩባንያዎች ጋር በሽርክና  እንደሚሰራ ገልጸዋል። ከአገር ውጭ የሚከውነው የመጀመሪያ ተሞክሮው ከሆነው ከዚህ ፕሮጀከት ከሚገኝ ትርፍ ኮርፖሬሽኑ 15 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። እንደ አቶ ጥንፉ ገለጻ በምስራቅ አፍሪካ በሚፈጠረው የትራንስፖርት መሰረተ ልማት በተለይም በመንገድ ግንባታና ጥገና ስራዎች፣ በግድብ፣ በጥልቅ ውሃ ጉድጓድና በተለያዩ ግንባታዎች ከአገር ውጭ ለመስራት ዕድል የሚፈጥርም ነው። ፕሮጀክቱ ኮርፖሬሽኑ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በሩዋንዳ ለማስተዋወቅ እገዛ ማድረጉንም ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ ከውሃ መሰረተ ልማት ባሻገር በመንገድ ግንባታም የሩዋንዳ መንግስት በሚያወጣቸው ጨረታዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛል። ይህ ፕሮጀክት ''በዓለም አቀፍ ጨረታ ውስጥ ገብተን ለመወዳደር እንድንችል ዕድል የፈጠረልን ነው'' ብለዋል አቶ ጥንፉ። የፕሮጀክቱ አፈጻጸም የተሻለ መሆን ከኮርፖሬሽኑ ጋር በሽርክና ከሚሰሩት በተጨማሪ ከሌሎች በዘርፉ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር መስራት የሚችልበትን ዕድል የሚያሰፋ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል። ኤምፒ እና ኤንፒዲ የተሰኙት ሃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ድርጅቶች በሩዋንዳ በውሃ መስኖ ግንባታ ስራ የተሰማሩ ናቸው። በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ለማሳደግ ኮርፖሬሽኑ ልምዱን በመቀመር በካበተ ልምድ፣ ሰራተኞችና ማሽነሪዎች ታግዞ በዓለም ዓቀፍ ጨረታዎች በመሳተፍ የቀጣናውን የግንባታ ዘርፍ ገበያ የመሸፈን ዕቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በአገር ውስጥ በርካታ የመንገድ፣ የመስኖ ግድብና ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ ይገኛል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም