የመከላከያ ሠራዊት ባካሄደው መሠረታዊ የአሰራር ማሻሻያ ስድስት የነበረውን ዕዝ ወደ አራት ዝቅ አደረገ

87
አዲስ አበባ  ታህሳስ 4/2011 የመከላከያ ሠራዊት ባካሄደው የመሠረታዊ የአሰራር ማሻሻያ ስድስት የነበረውን ዕዝ ወደ አራት ዝቅ አደረገ። በማሻሻያው የተዋቀሩት አራቱ ዕዞች የሰሜን፣ የደቡብ፣ የምሥራቅና የምዕራብ ናቸው። ከዚህ በፊት የነበረው የክፍለ ጦርና የብርጌድ ቁጥርም ዝቅ ያለ ሲሆን በተሻሻለው መዋቅርም ብቃት ያላቸው ክፍለ ጦሮችና ብርጌዶች ተደራጅተዋል። እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱ የምድር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል፣ የአየር ኃይልና የባህር ኃይል በመሠረታዊ የአሰራር ማሻሻያው እንዲደራጁ ተደርጓል። የልዩ ዘመቻዎች ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሞላ ኃይለማርያም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ማሻሻያውን መሠረት በማድረግ ሁሉንም ብሔሮች የሚወክል አዳዲስ አመራር ምድባ ተካሂዷል። የባህር ኃይልን ለማደራጀት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ሌተናል ጄኔራል ሞላ ጥናቶችን እና ሌሎች ተግባራትን  የሚያከናውን ቡድንም መደራጀቱን ተናግረዋል። በተመሳሳይ የምድር ኃይል በቅርብ ጊዜ እንደሚደራጅም ገልፀዋል። በዚህም ሳይንሳዊ አደረጃጀት ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል። እንደ ሌተናል ጄኔራል ሞላ ገለጻ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በአስተማማኝ ሰላም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረው ከፍተኛ ሠራዊት ወደ ተለያዩ ቦታዎች እንዲመደብ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም