የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ አራት ዓመት ይፈጃል - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ አራት ዓመት ይፈጃል
አዲስ አበባ ታህሳስ 4/2011 የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ የማጠናቀቁ ስራ አራት ዓመታትን እንደሚወስድ ተገለጸ። የግድቡ ግንባታ 80 ቢሊዮን ብር እንደሚያስወጣ የተገለጸ ቢሆንም አሁን በሚገኝበት ደረጃ 98 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተነግሯል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጀነር ስለሺ በቀለ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃም በላይና የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮን ያሳተፈና በግድቡ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል። የጥራት ችግር፣ ስራዎችን በጊዜ አለማከናወንና የተዛባ የተቋማት ግንኙነት ለግድቡ ግንባታ መጓተት ዋነኞቹ ማነቆዎች መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል። ግድቡ አሁን ባለበት ሂደት የሲቪልና የሃይድሮ ሜካኒካል ስራዎች በቅደም ተከተል 82 እና 25 በመቶ አፈጻጸም ሲኖራቸው የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 65 በመቶ ላይ ይገኛል። የሲቪል ስራው በተከናወነበት ልክ ክፍያ የተፈጸመ ሲሆን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውን የከወነው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ በ25 በመቶ አፈጻጸም የ65 በመቶ ክፍያ መውሰዱ ተገልጿል። የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንደተናገሩት የግድቡን ዘመን ተሻጋሪነት ለማረጋጋጥ እስካሁን የተሰሩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች "ብይድ ሳይቀር" ጥራታቸው እየተፈተሸ ነው። በዚህ መሰረት ግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት ለመጀመር ሁለት ዓመት ይወስድበታል ነው ያሉት። የግድቡን አጠቃላይ ግንባታ ከአራት ዓመት በኋላ ማለትም በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2022 ለማጠናቀቅ መታቀዱንም አክለዋል። አስካሁን ለግድቡ ግንባታ 98 ቢሊዮን ብር የወጣ ሲሆን ለወጪው መናር የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው የራሱ ሚና መጫወቱን ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አብርሃም በላይ ግድቡን በሚመለከት ከዚህ ቀደም ፖለቲካዊና ሙያዊ ጉዳዮች የሚጋጩና በጋራ የሚሰሩ ተቋማት ትስስርም ደካማ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህ የተዛባ ግንኙነት መቆሙንም ዋና ስራ አስኪያጁ ዶክተር አብርሃም በላይ ጠቁመዋል። የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ በመሆኑ የግድቡ ግንባታ የቆመ የሚመስላቸው አካላት እንዳሉ የጠቆሙት ዶክተር አብርሃም ግንባታው 'ለደቂቃም ሳይቋረጥ እየተከናወነ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል' ነው ያሉት። "ዜጎች በግድቡ ላይ ያላቸው መተማመን እንዲመለስ ጠንክረን ሰርተን ውጤት ለማሳየት እየተጋን ነው" ሲሉም አክለዋል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ከግንባታው ጎን ለጎን ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው የሶስትዮሽ ድርድር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ባለፈው መስከረም አጋማሽ አገራቱ በግድቡ ውሃ ሙሊት ላይ ፍሬያማ ድርድር ማድረጋቸውን በመጠቆም።