ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ የ15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ የ15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘች
አዲስ አበባ ታህሳስ 4/2011 የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የሚውል የ15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሰጠ። ድጋፉ በአራት ክልሎች ማለትም በአማራ ቡሬ፣ በኦሮሚያ ቡልቡላ፣ በትግራይ ቤከርና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ይርጋለም ለተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ይውላል ተብሏል። የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና በኢትዮጵያ የአፍሪካ ልማት ባንክ ተጠሪ ዶክተር አብዱል ካማራ ዛሬ የድጋፍ ስምምነት ፈርመዋል። አቶ አህመድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአምራቹና በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መካከል የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን በማሳለጥ አካታችና ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ እንደሚያስችሉም ተናግረዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ያቀረበው ድጋፍ አገሪቱ በዘርፉ የጀመረቻቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በግብዓት ለማጠናከር ያግዛል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ይህ ድጋፍ በአቅም ግንባታና ውጤታማ አስተዳደርና ትብብር በመፍጠር ቀጣይነት ላለው የአግሮ ኢንዱስትሪ ልማት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል። ባንኩ ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ሚኒስትር አህመድ ኢትዮጵያ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል። ዶክተር አብዱል ካማራ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ 'እንደግፋለን' ነው ያሉት። የአፍሪካ ልማት ባንክ በአጠቃላይ ለኃይል አቅርቦት፣ ለትራንስፖርት፣ ለውሃ አቅርቦት፣ ለግብርና፣ ለአስተዳደርና ለሌሎች መሰረተ ልማቶች ማስፋፊያ የሚውል የ1 ነጥብ 89 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል። ለተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የተደረገው የ15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍም የዚሁ አካል መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ከግብ እንዲደርስ ባንኩ ድጋፉን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።