የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ሊሻሻል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ሊሻሻል ነው
አዲስ አበባ ታህሳስ 4/2011 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ሊሻሻል መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የአዋጁ መሻሻል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተደጋጋሚ የሚታየውን የኦዲት ክፍተት ለማቃለልና ግልጽ አሰራር ለመፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደርና ሪፎርም ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተፈራ ለኢዜአ እንዳሉት በዩኒቨርስቲዎች የፋይናንስ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ችግር መኖሩ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል። በሥራ ላይ ያለው የከፍተኛ ትምህርት አዋጁ ቁጥር 650/2001 ዩኒቨርስቲዎቹን በአዋጁ ላይ በተቀመጠው የፋይናንስ አስተዳደር መመራት እንዳለባቸው ይደነግጋል። በአዋጁ አንቀፅ 66 እና 67 በተቀመጠው መሰረትና በህግ ከተፈቀዱ ሌሎች ምንጮች ገቢዎችን ማሰባሰብ እንደሚችልም ተቀምጧል። ይሁንና ዋና ኢዲተር መስሪያ ቤት ዩኒቨርስቲዎች እንደማንኛውም የመንግስት ባለበጀት መስሪያቤት መተዳደር ያለባቸው በፋይናንስ ህጉ መሆኑን ያስቀምጣል። በከፍተኛ ትምህርት አዋጁና በፋይናንስ አዋጁ ላይ የተፈጠረው ክፍተት ታድያ ተቋማቱን ለኦዲት ችግር እንዲጋለጡ ማድረጉን አቶ ጌታቸው አብራርተዋል። የሚሻሻለው አዋጅ ከሌሎች አዋጆች ጋር ተቃርኖ እንዳይኖረው ሆኖ የተስተካከለ በመሆኑ እስካሁን እየተፈጠሩ የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እንደሚረዳም ነው አቶ ጌታቸው ያብራሩት። ረቂቅ አዋጁ ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን በቅርቡም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃለ። ዩኒቨርስቲዎችን በየዓመቱ የኦዲት ግኝት ሆኖ ከሚወጣባቸው ጉዳዮች አንዱ ተመን የሌለው ክፍያ መሆኑን የሚያነሱት ጄኔራል ዳይሬክተሩ እስካሁን ተመን ላልነበራቸው ክፍያዎች በዚህ ዓመት ተመን እንዲወጣላቸው መደረጉንም አንስተዋል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በ2009 በጀት ዓመት ባወጣው የኦዲት ግኝት 6 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስራው ባህሪ ቋሚነት ያለው መሆኑ እየታወቀ በፐፕሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር ያልተፈቀደ የኮንትራት ሰራተኞችን በመቅጠር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የደመወዝ ክፍያ መክፈላቸውን በሪፖርቱ አመላክቷል። ሌሎች 13 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ሁለት መስሪያቤቶች ተመራማሪዎች ጥናት ላቀረቡበት፣ ለፈተና ግምገማ፣ የማስተርስ እና ፒ ኤች ዲ ተማሪዎችን ለፈተኑበትና ለገመገሙበት፣ ለመመረቂያ ጽሁፍ ማማከር ስራዎች በመንግስት የተፈቀደ የክፍያ መመሪያና የክፍያ ተመን ሳይኖር ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያዎች መፈጸማቸው በኦዲት ተረጋግጧል።