የኬሚካል ኢንዱስትሪው የሚመራበት ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የኬሚካል ኢንዱስትሪው የሚመራበት ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ ታህሳስ 4/2011 የኬሚካል ኢንዱስትሪው የሚመራበት ረቂቅ ፍኖተ ካርታ በአዲስ መልክ ተዘጋጀ። ፍኖተ ካርታው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት /ዩኒዶ/ ድጋፍ በተካሄደ አገር አቀፍ ጥናት መዘጋጀቱን የገለጸው የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ነው። የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፍኖተ ካርታው በቅርቡ ሥራ ላይ ይውል ዘንድ ከድርጅቱ የልዑካን ቡድን ጋር ዛሬ ተወያይተዋል። ይህን ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ከአንድ ዓመት በፊት ችግሮችና መፍትሄውን የሚያመላክት በጥናት የተደገፈ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል። ለጥናቱ ያስፈለገው የ400 ሺህ ዶላር ወጪ በዩኒዶ የተሸፈነ ሲሆን አገሪቷ በቀጣይ በመስኩ ውጤታማ ልትሆን የምትችልባቸውን መንገዶች ያመላከተ ነው ተብሏል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደዬሳ ለታ እንደገለጹት ጥናቱ በኢትዮጵያ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሰፊ የቴክኖሎጂና የእውቀት ክፍተት መኖሩን አሳይቷል። የእውቀት ክፍተቱን ለመሙላት በዩኒቨርሲቲዎች፣ በቴክኒክና ሙያና ትምህርትና ስልጠና ሂደት ምን አይነት የሰው ኃብት ልማት ሊኖረን ይገባል፣ የትኛው አይነት ሙያ በየትኛው ጊዜ ያስፈልጋል የሚሉት ጉዳዮች በፍኖተ ካርታው መዳሰሳቸውን አብራርተዋል። ጥናቱን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀው አዲሱ ፍኖተ ካርታም በምን አይነት መልኩ፣ በየትኛው ጊዜ፣ ምን አይነት ቴክኖሎጂና ዕውቀት ይዘን መሄድ እንዳለብን 'አቅጣጫዎችን አሳይቷል' ነው ያሉት። ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ልማት ጋር በተያያዘ በአካባቢ ጥበቃና ደህንነት አገሪቷ ከምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ጋር ማጣጣም የሚቻልበትን አቅጣጫም ያመላከተ ነው። ''በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ያልታገዘ የኢንዱስትሪ ልማት ለአገር ኪሳራ ነው'' ያሉት አቶ ደዬሳ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽና ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እንደሚያደርግ አክለዋል። በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ግብዓት የማሰባሰብ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ታትሞ ለሚመለከታቸው አካላት 'ይሰራጫል' ብለዋል። ኢንዱስትሪውን በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የባለሙያዎች ስልጠና በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ለመስጠት ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ባሻገር በአገሪቷ ኢንዱስትሪዎች መካከል የተቀናጀና ተመጋጋቢ ልማት እንዲኖር ይሰራል። እንደ አቶ ደዬሳ ገለጻ በኬሚካል ምርት፣ ማጓጓዝ፣ ማከፋፈልና ገቢና ወጪ ሂደቶች ላይ ሊኖሩ የሚገባቸው አሰራሮች በዝርዝር መቀመጣቸው ውጤታማ እንደሚያደርግ ታምኖበታል። የኢንዱስትሪው ተቋማዊ አደረጃጀት በግልጽ የተቀመጠ በመሆኑ ፍኖተ ካርታው ስኬታማ ስራ መከወን ያስችላል ነው ያሉት።