ቀጥታ፡

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ግልፅነትና ተጠያቂነት የተላበሱ አሰራሮች እንዲሰፍኑ ድርሻቸውን መጫወት አለባቸው

አዳማ  ታህሳስ 4/2011 የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች ግልፅነትና ተጠያቂነት የተላበሱ አሰራሮች እንዲሰፍኑ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ድርሻቸውን መጫወት እንደሚጠበቅባቸው የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አመለከተ። ባለሙያዎቹ ከፌዴራልና ከክልሎች ከተውጣጡ የዘርፉ ሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር የሉሜ አዳማ የኅብረት ሥራ ዩኒዬንን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ አህመድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ባለሙያዎቹ የተቋማቱ አሰራር ግልፅና ተጠያቂነት የተላበሰ እንዲሆን ሚናቸው ጉልህ ነው። ባለሙያዎቹ የተቋማቱ ኦዲት አሰራርና የሂሳብ አያያዝ፣ግልፅነትና ተጠያቂነት የሚታይበት አገልግሎት ለአባሎቻቸው በመስጠትና ዘርፉ ብቃት ባለው የሰው ኃይል በመምራት የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። ዩኒየኖቹ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት እንዲሸጋገሩና በአገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ድርሻቸውን እንዲጫወቱ በማገዝ ባለሙያዎቹ ሚና እንዳላቸውም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። የሉሜ አዳማ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብዲ በበኩላቸው ዩኒዬኑ የአባላቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ምርቱን ከመሰብሰብ ባለፈ የዱቄት ፋብሪካ በማቋቋም እሴት ጨምረው ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል። ዩኒየኑ የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ለማቋቋም ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት አሸናፊዎች እየተለዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዩኒዬኑ ከ400 በላይ የዳልጋ ከብቶችን በማድለብ ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ፣በቀጣይም ለውጭ  ገበያ ለማቅረብ የአዋጭነት ጥናት እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። ከሦሰት የመድህን ኩባንያዎች ከ25 ሚሊዮን ብር  በላይ አክሲዮኖች በመግዛት ዘርፈ ብዙ ኢንቨስትመንትና ንግድ ውስጥ መግባቱንም አስረድተዋል። ዩኒየኑ በአሁኑ ወቅት ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያፈራ ሲሆን፣103 መሠረታዊ ማህበራትና ከ60 ሺህ በላይ አባ ወራዎች አባላት አሉት። ዩኒዬኖቹ የመሠረታዊ ማህበራትን አቅም በመገንባት፣ ዘላቂ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ወደ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ለመሸጋገር መሥራት እንደሚገባቸው በጉብኝቱ ላይ የተካፈሉት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቅሱ 388 ዩኒየኖች ይገኛሉ።ዩኒየኖቹ የግብርና ምርቶችን ከመሰብሰብ ባለፈ፤ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንቨስትመንት በመሰማራት እሴት ጨምረው ለገበያ እንደሚያቀርቡ የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም