ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የ2018 የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያን የ2018 የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት ይፋ አደረገ። የ2018 ብሔራዊ የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ሂደት አካታችና ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲያስገኙ ሆነው መመራት እንዳለባቸው ያሳያል። ይህ ማለት የሰብዓዊ ልማትን የሚደግፉ፣ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ለሁሉም የሚያከብሩ፣ ልዩነቶችን የሚያጠቡ ስልቶችና የዜጎችን ምርጫዎች የማስፋት ግብ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ልማት ከትምህርትና ከገቢ ንዑስ አመላካቾች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው አማካይ የሰው ዕድሜ ሲሆን የዚህ መነሻም የጤናው ዘርፍ ውጤቶች መሆናቸው ተገልጿል። ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ንዑስ አመላካች ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ዝቅተኛ የሰብዓዊ ልማት አመላካች ደረጃ ካላቸው ሶሪያ፣ ሴኔጋል፣ ማዳጋስካር፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያና ሶሎሞን ደሴት አገራት መካከል አንዷ ሆናለች። አገሪቱ በትምህርት አመላካች የሰብዓዊ ልማት ዝቅተኛ ያደረጋት በንጽጽር የትምህርት እድል አለማግኘት መሆኑ ተቀምጧል። እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር 2012 እና 2013 ጀምሮ በሁሉም ክልሎች የሰብዓዊ ልማት አመላካች ጤና ዕድገት ያሳየ ሲሆን ሀረሪ በጤናው ንዑስ አመላካች ወደኋላ የቀረ ብቸኛው ክልል መሆኑን ሪፖርቱ አስቀምጧል። የትምህርት ስኬት መሻሻል ቢያሳይም በፆታ እንዲሁም በገጠርና በከተማ መካከል ያለው ምጣኔ አሁንም ዝቅተኛ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም በ2013 ዕድሜያቸው 10 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ 32 በመቶ ወንዶች እና 51 በመቶ ሴቶች የትምህርት እድል አልነበረም። ከዚሁ ጋር እድሜያቸው በትምህርት መሆን ከሚገባቸው ውስጥ 1 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ቢያንስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቀዋል። የትምህርት ወጪ በተነፃፃሪነት ከፍተኛ ቢሆንም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በአገሪቱ ውጤታማነቱ አሁንም ዝቅተኛ እንደሆነ፣ በተለይም በትምህርት ጥራት ላይ ጫና መፍጠሩን ሪፖርቱ አመላክቷል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት እ.አ.አ በ2000 የነበረው ዜሮ ነጥብ 283 ውጤት በ2015 ዜሮ ነጥብ 448 ሆኖ ተመዝግቧል፤ ይህም ኢትዮጵያን ከ188 አገራት 174ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አስችሏታል። በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ሚስተር አኒያስ ቹማ ሪፖርቱ ለፖሊሲ አውጪዎች በግብዓትነት የሚያገለግል መሆኑን ጠቅሰዋል። ለአካታችና ለዘላቂ ሰብዓዊ ልማት እንደ አንድ ማሳኪያ መሳሪያ የተፋጠነና ተወዳዳሪ የኢንዱስትሪ እድገት ለማምጣት ሪፖርቱ ተጨባጭ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን እንደሚያቀርብም ነው የገለጹት። የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው አደም በበኩላቸው በጤናው ዘርፍ የተመዘገበው አበረታች ውጤት በትምህርትም  እንዲደገም አገሪቱ የተለያዩ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ገልፀዋል። የጥናቱ ውጤት የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የሰራው በመሆኑ 'ምን ያህል መረጃዎችን ተጠቅሟል የሚለውን መርምረን በትብብር እንሰራለን' ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም