ተደጋጋሚ የኦዲት ክፍተት ያለባቸው መስሪያ ቤቶች ክፍተቶቻቸውን በጋራ ለማረም መከሩ

አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 ተደጋጋሚ የኦዲት ክፍተት ያለባቸው የመንግስት ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች ክፍተታቸውን በጋራ ማረም በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስተባባሪነት የተመሰረተው የባለድርሻ አካላት ፎረም የ2011 በጀት ዓመት የጋራ እቅዱን ዛሬ ገምግሟል። ከደንብና መመሪያ ውጪ የሚፈጸሙ ግዥዎች፣ ያልተገባ ክፍያ፣ ከተሰብሳቢ ሂሳብና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚታዩ የኦዲት ክፍተቶች እንዳይደገሙ ባለድርሻ አካላቱ መፍትሄ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል። በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ገለታ ስዩም እንዳሉት''ሁሉንም ተቋማት ወደ ክስ ሄደን እርምጃ መውሰድ ያለብን በክሱ ብቻ ነው ወይ ሌላ አስተዳደራዊ የሆኑ ስራዎችን መስራት እንዴት እንችላለን የተዘጋጀው ሪፖርት ቀርቦ የእያንዳንዱ ተቋማት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ባህሪ ተለይቶ የሚመለከታቸው ተቋማት ተሰብስበው ውይይት ተካሂዶበት ከክስ በፊት ያሉት እርምጃዎች እንዴት ሊወሰዱ ይችላሉ። ምክንያቱም 170 ተቋማት በክስ ብቻ ውጤት አይመጣም መለስተኛ የሆኑትን አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ማምጣት ይቻላል ብዬ ስለማስብ ነው።'' ''ከእኛ አኳያ በግልጽ ያስቀመጥነው ነገር አንደኛ ያለፉ ግኝቶችን የማስተካከል ነው፣ ሁለተኛ እነዚህ ግኝቶች ደግመው እንዳይከሰቱ የማድረግ ስራ መስራት ነው '' ያሉት ደሞ የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ናቸው፡፡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደርና ሪፎርም ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተፈራ በበኩላቸው ''የዩኒቨርሲቲዎችን ስራ ስናይ በጣም አስቸጋሪ ጉዳዮች እንዳሉ መረዳት ጠቃሚ ነው የሚሆነው፤ ፈጥነን እሱ ላይ ካልገባን በዩኒቨርሲቲዎቹ ላይ ብቻ ይሄንን ብናወርደው ዘላቂ መፍትሄ ያገኛል ብዬ አላስብም'' ብለዋል፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴር ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝት ማስተካከያ መርሀ ግብር እንዲያዘጋጁና የተደረገውን ማስተካከያም በመስሪያ ቤቱ የውስጥ ኦዲተሮች በመከታተል ውጤቱን ለቋሚ ኮሚቴው ለማሳወቅ አቅዷል። ለረዥም ጊዜ የቆዩ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በደንብና መመሪያ መሰረት ከመዝገብ መሰረዝ ያልተቻሉትን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማሳወቅ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለማድረግም እንዲሁ። የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግም የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝትን መሰረት በማድረግ ከህግ ጥሰት ጋር የተያያዙ የኦዲት ግኝቶችን በፍጥነት በመለየት በወንጀል የሚጠየቁ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ በእቅዱ አስቀምጧል። የገቢዎች ሚኒስቴር የኦዲት ግኝቶችን ችግር በተሟላ መልኩ ለመፍታት የሚረዱ ጥናቶች ለማካሄድና በባለስልጣኑ ተጠሪ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ላይ የኦዲት ግኝት የሆኑ ጉዳዮችን በማስተካከል ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙበትን የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት አቅዷል። የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገለሶ ዋና ኦዲተር ተቋማትን ኦዲት የሚያደርገው የአገሪቷ ሀብትና ንብረት በህግና ደንብ እንዲመራ ለማድረግ መሆኑን አውስተዋል። ይህን በአግባቡ ለመምራት ተቋማት በኦዲት ግኝቶች ላይ የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት። መንግስት ከፍተኛ በጀት የሚመድብላቸውና አገሪቷን በኢኮኖሚ ጫና ውስጥ የሚከቱ የሙስና ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መታየት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ፎረም የተመሰረተው በፌዴራል ዋና ኢዲተር የሚቀርቡ የኦዲት ሪፖርቶች ላይ ተጨባጭ መፍትሄ ለማምጣትና የተጠያቂነት አሰራር ለማስፈን ታስቦ ነው። የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህት ተቋማት ሚኒስቴር፣ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎች እንዲሁም ፕላን ኮሚሽን የፎረሙ አባላት ናቸው። ተቋማቱ የ2011 በጀት ዓመት እቅዳቸውን ለቋሚ ኮሚቴው የላኩት ባለፈው ሐምሌ ቢሆንም ቋሚ ኮሚቴውና አስፈጻሚ አካላትን በአዲስ መልክ የማደራጀት ስራ ሲሰራ ጊዜ መውሰዱ ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም