በአዲስ አበባ ቅዳሜና እሑድ ይደረጋል የሚባለው ሠላማዊ ሰልፍ እውቅና የለውም - የአዲስ አበባ ፖሊስ

61
አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 በመዲናዋ በመጪው ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳል የሚባለው ሠላማዊ ሰልፍ እውቅና የሌለው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። አንዳንድ ግለሰቦች ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ሠልፉ በከተማ አስተዳደሩም ሆነ በፖሊስ ኮሚሽኑ እውቅና እንደሌለው ገልጿል። ኮሚሽኑ አንዳንድ ግለሰቦች በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ስፍራዎች ከፀጥታ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች ሊቀረፉ ይገባል፣ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደግፋለን የሚሉ መነሻ ሃሳቦችን በመያዝ ቅዳሜ ታህሳስ 6 እና እሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም በመዲናዋ ሰልፍ ለመውጣት መዘጋጀታቸውን መረጃ ደርሶታል። የኮሚሽኑ ኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለአዜአ እንደገለጹት ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህገ-መንግስታዊ መብት ቢሆንም በተጠቀሱት ቀናት ሰልፍ እንወጣለን የሚሉ ወገኖች የሰልፉን መነሻና መድረሻ፣ የአስተባባሪዎችን ማንነትና አድራሻ እንዲሁም መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ለሚመለከተው አካል አላሳወቁም። በመሆኑም ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ እንደሚቸገር ነው የገለጹት። ኮሚሽኑ ቅዳሜና እሁድ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን አስቀድሞ ፕሮግራም የያዘ በመሆኑ ሰልፍ እናደርጋለን ለሚሉ ወገኖች ጥበቃ ለማድረግ የሰው ኃይል ችግር ሊያጋጥመው እንደሚችልም ነው የተናገሩት። የተባለው ሠልፍ በከተማ አስተዳደሩም ይሁን በፖሊስ ኮሚሽኑ እውቅና እንደሌለው ሰልፉን የጠሩ ወገኖች፣ የሚመለከታቸው አካላትና  ህብረተሰቡም እንዲገነዘቡለት 'ኮሚሽኑ መልዕክቱን አስተላልፏል' ብለዋል ኮማንደር ፋሲካ። ይህን መልዕክት በመተላለፍ ሠልፍ የመውጣት እንቅስቃሴ የሚደረግ ከሆነ ፖሊስ በህግ አግባብ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም