በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ 47 ሀገራትን ሊያግዝ የሚችል አዲስ የትብብር ማእቀፍ ትግበራ ሰነድ ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ 47 ሀገራትን ሊያግዝ የሚችል አዲስ የትብብር ማእቀፍ ትግበራ ሰነድ ይፋ ተደረገ
ፖላንድ ታህሳስ 2/4/2011 በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ 47 ሀገራትን ሊያግዝ የሚችል አዲስ የትብብር ማእቀፍ ትግበራ ሰነድ ይፋ ተደረገ፡፡ በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ 47 ሀገራትን ያቀፈውና LDC/List developed countries/የሚል አህጽሮተ ቃል ባለው ቡድን ኢትዮጵያ የሊቀመንበርነት ቦታን በመያዝ በሀገራቱ ላይ የሚስተዋሉ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለዓለም በማሰማት ትመክራለች፡፡ በፖላንድ ሀገር 24ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ለሀገራቱ ይጠቅማል የምትለውን ጉዳይ ከሀገራቱ ጋር በመመካከር የሚያነሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች በመቀመር ለበለጸጉ ሀገራት ድምጿን እያሰማች ትገኛለች ፡፡ በትናንትናው እለትም 47 በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት፣ የበለጸጉ ሀገራት፣ የሲቪክ ማህበራትና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በጉዳዩ ላይ ተመክሯል፡፡ በዚህን ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የአካባቢ፣የደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ የፓሪስ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት በመስኩ የተደቀነባቸው ችግሮች በተባበረ ክንድ ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አያይዘውም የአየር ለውጥ ጉዳይ የበለጸጉ ሀገራትንም እየጎዳ የሚገኝ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባ ገልጸው፤ ይህም ችግሩ በአፋጣኝ እልባት ካልተሰጠው ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላሉ ሀገራት ጉዳቱን የከፋ ሊያደርገው ይችላል ብለዋል፡፡ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሁሉም ሀገራት የሚችሉትን ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኙ የዩናይትድ ኪንግደም ዩኬ ፣ የጀርመን እንዲሁም የአይርሽ ተወካዮች ለሀገራቱ የቻሉትን ድጋፍ ለማድረግ ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡ የአከባቢ፣የደንና ንብረት ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ ሀገራቱ ለሰጡት ፈጣን ምላሽም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢትዮጵያዊው አቶ ገብሩ ጀምበሩ አዲስ የጋራ የትብብር ማእቀፉን የትግበራ ሰነድ ዝርዝር ገለጻ በማድረግ ሀገራቱ እንዲጠቀሙበት ይፋ አድርገዋል፡፡ የLDC ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ገብሩ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታም በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በፓሪስ ስምምነት መተግበር የሚገባቸውን ስራዎች እንዲልኩ ተደርገው እቅዶቻቸውን ባየንበት ወቅት ሀገራቱ ችግሮቻቸውን በሚፈታና በባለቤትነት የመሩት አለመሆኑን የሚያመላክቱ ጉዳዮች ተመልክተናል ብለዋል፡፡ ሀገራቱ የተሻሻለ የአቅም ግንባታ ስልጠና አግኝተው ቢሆን የተሻለ አድርገው ሊሰሩት ይችሉ እንደነበርም ተናግረዋል። አሰራሩን በማዳበር ረገድም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ክፍተቱን በመለየት መስራት ለሚገቧቸው ጉዳዮች አጋዥ እንዲሆኑ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ የአገራቱ የአቅም ግንባታው፣ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል፡፡ ለፓሪሱ ስምምነት ግብዓት እንዲሆንም ብዙ ሀገሮች ተግባራዊ ያላደረጉ በመኖራቸው ችግሩን ተገንዝበው በአግባቡ እንዲመለከቱት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ በአጠቃላይ ከ2020 ጀምሮ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው የትብብር ማእቀፍ ትግበራ ሰነድ ተግባራዊ ሲደረግ በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት ያላቸውን የክህሎት፣ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂና ክፍተቶች በተደራጀ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የበለጸጉ ሀገራት በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራትን ለመደገፍ በ2020 ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለአየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከ2025 ጀምሮ ደግሞ ከዚያ በላይ ድጋፍ ካላደረጉ ዓለም አስጊ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ የፓሪሱ ስምምነት ማእቀፍ ይገልጻል፡፡