በቦንጋ የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችና ምርቶች የቀረቡበት ዐውደ ርዕይ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በቦንጋ የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችና ምርቶች የቀረቡበት ዐውደ ርዕይ ተካሄደ
ሚዛን ታህሳስ 2/2011 የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችና ምርቶች የቀረቡበት ዐውደ ርዕይ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል። ''ፊድ ዘ ፊውቸር'' በተሰኘ ድርጅት በተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ላይ አርሶ አደሮችና በግብርና ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች ተካፍለውበታል። በድርጅቱ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሚስተር ኢያን ቸስተርማን እንደገለጹት ዐውደ ርዕዩ ግብዓት አቅራቢዎችና ነጋዴዎች የአርሶ አደሩን ፍላጎት በመረዳት ግብዓቶችን በወቅቱ እንዲያቀርቡለትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ ግብዓት አቅራቢ ድርጅቶች ወቅትን መሠረት ያደረገ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርታማነት እንዲጨምርና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሰሩም ጠይቀዋል፡፡ ድርጅቱ በአራት ክልሎች ቴክኖሎጂ አቅራቢዎችንና አርሶ አደሮችን በማገናኘት የገበያ ትስስር እየፈጠረ መሆኑንም አስተባባሪው አመልከተዋል። ከካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ አርሶ አደር ሰለሞን አየለ ከብቶቻቸውን ለገንዲ በሽታ የሚዳርገውን የቆላ ዝንብ የሚከላከሉበት መድኃት በዐውደ ርዕዩ ላይ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ''አካባቢያችን ቆላማ በመሆኑ ከብቶቻችን በተለያዩ በሽታዎች ይጠቃሉ'' ያሉት አቶ ሰለሞን፣ መድኃኒቱ ከብቶቻቸው የሚገጥማቸውን ጉዳት እንደሚቀንስላቸው ተናግረዋል፡፡ የካፋ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ማግኔቾ በዞኑ በግብርና ላይ ትኩረት ያደረጉ ዐውደ ርዕዮች መካሄዳቸው ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የጎላ ድርሻ አላቸው ብለዋል። መንግሥት የግብርና ግብዓቶች በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ለማጠናከር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል፡፡ በዐውደ ርዕዩ የተሻሻሉ ማረሻዎች፣የግብርና መሣሪያዎች፣የእንስሳት መድኃኒትና የግብርና ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል፡፡