ሠራተኞቹ ለሥራ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እየቀረበላቸው ባለመሆኑ እለታዊ ተግባራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
ሠራተኞቹ ለሥራ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እየቀረበላቸው ባለመሆኑ እለታዊ ተግባራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ አይደለም
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 አዲስ አበባ የሚገኘው ግዮን ሆቴል ሠራተኞች ለሥራ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እየቀረበላቸው ባለመሆኑ እለታዊ ተግባራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ እንዳልሆነ ገለፁ። ችግሩ መኖሩን የተቀበለው የሆቴሉ አስተዳደር በበኩሉ የተጠቀሰው ቅሬታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታ ቃል ገብቷል። የመንግሰት የልማት ድርጅት የሆነው ዕድሜ ጠገቡ ግዮን ሆቴል እንግዶች የሚጠቀሙባቸው አልባሳት ማጠቢያ ማሽን፣ የሠራተኞች የሥራ አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ መሰረታዊ የሆቴል አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን እያቀረበ አይደለም። ሰራተኞቹ የስራ ልብስ፣ ጫማ፣ ጓንትና ሌሎች አስፈላጊ የሥራ መገልገያ ቁሳቁስ ከቀረበላቸው ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም የተነሳ በሆቴሉ በቤት አያያዝ፣ በመስተንግዶ፣ የአልባሳት ንጽህና፣ በእቃ ግምጃ ቤት፣ በጉልበት አገልግሎትና ሌሎች የሥራ ክፍሎች የተመደቡ ሰራተኞች ሥራዎቻቸውን የሚያከናውኑት ኋላቀር፣ ደህንነቱ ባልተጠበቀና አድካሚ በሆነ መንገድ ነው። ይህም የሆቴሉ አገልግሎት ጥራት እንዲዳከም ከማድረጉም በላይ በሰራተኛው ላይ ከፍተኛ ጫና እየተፈጠረ መሆኑን ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የሆቴሉ ሰራተኞች ለኢዜአ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የሆቴሉ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች በመበላሸታቸው በክፍሉ የተመደቡት ባለሙያዎች እጥበት የሚያከናውኑት በእጃቸው መሆኑን ይገልፃሉ። በመዋኛ ስፍራ የተመደቡ የህይወት አድን ሰራተኞችም የድርጅቱ አርማ ያለበት ትጥቅ የሌላቸው በመሆኑ ተጠቃሚዎች ሰራተኞቹን ለመለየት እንኳ እየተቸገሩ መሆኑንም ጠቁመዋል። የስራ ደረጃ ዕድገት በትውውቅና በዝምድና መሆን፣ ዝቅተኛ ደሞዝ፣ በየክፍሉ ባለው የሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ የስራ ጫና መኖር፣ ከስራ ሰዓት ውጪ ያለ ትርፍ ሰዓት ክፍያ መስራት በሰራተኞቹ የቀረቡ ቅሬታዎቸ ናቸው። ድርጅቱ በኪሳራ ላይ ነው በሚል ምክንያት ጉርሻና የደሞዝ ጭማሬ መከልከልም ሌሎቹ በሰራተኞቹ የቀረቡ ቅሬታዎች ናቸው። ያሉትን ችግሮች በግልጽ በሚናገሩ ሰራተኞች ላይ ከተቀጠሩበት የስራ መደብ ማንሳትን ጨምሮ የተለያየ ጫና መፍጠርም እንዲሁ። በግዮን ሆቴሎች ድርጅት መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዜና በላይነህ ሰራተኞቹ ያቀረቡት የቁሳቁስና መሳሪያ ችግር እንዲፈታ ለሚመለከተው የአስተዳደር አካል ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልፀዋል። "ችግሩ የተፈጠረው ቀደም ሲል ድርጅቱ ገጥሞት በነበረው የገንዘብ እጥረት ነው፤ በአሁን ወቅት ግን የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁሶችን ለመግዛት የጨረታ ሂደት ተጀምሯል" ሲሉም ተናግረዋል። በልብስ መስጫ ክፍል ያሉት ማሽኖች ብልሽት ችግር እንዲፈታ ከድርጅቱ ኃላፊዎች ባለፈ ለድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል። ሆኖም በቅርቡ የቦርድ አባላቱ መቀያየራቸውን ገልጸው በዚሀ ሳቢያ ፈጣን ምላሽ አለመገኘቱን ጠቅሰዋል። እንዲያም ሆኖ ማህበሩ ክትትል እያደረገ ነው ይላሉ። እንደ አቶ ዜና ገለጻ በሰራተኞች ሕብረት ስምምነት ላይ አንድ ሰራተኛ የዲስፕሊን ጥሰት ካልተፈጸመ በስተቀር ከደረጃው ዝቅ አድርጎ መመደብ አይቻልም። የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ እሸቴ በበኩላቸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ተፈጥሮ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የሆቴሉ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ እንደነበር ጠቅሰው በዚህም ሳቢያ የሆቴሉ ገቢ በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ነበር ብለዋል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ሆቴሉን ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድረግም ለተከናወኑት የማሻሻያ ግንባታዎችም ከፍተኛ ወጪ መደረጉን አብራርተዋል። የስራ ልብስንና ማጠቢያ ማሽኖችን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁሶች ግዢ የዘገየውም በዚሁ የገንዘብ እጥረት ምክንያት መሆኑን ተናገረዋል። ያም ሆኖ በዚህ ዓመት የሆቴሉ ገቢ እየጨመረ በመምጣቱ ቁሳቁሶቹን ለመግዛት የጨረታ ሂደት እየተከናወነ ነው ይላሉ። በልብስ መስጫ ክፍል ማሽኖች ያልተሟሉት የመለዋወጫ መሳሪያዎችን በአገሪቱ በነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ በፍጥነት ከውጭ ለማስመጣት ባለመቻሉ እንደሆነም ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ማሽኖቹን ከውጭ አገር በማስመጣት ለማስገጠም ከኩባንያዎች ጋር እየተነጋገርን ነው ፤ " ችግሩ በአጭር ግዜ ውስጥ ይፈታል፤ የመሳሪያዎቹ እጥረት በሰራተኛው ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን እገነዘባለሁ፤" ነው ያሉት። የደሞዝ ጭማሬ ጥያቄው ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን አንስተው የደሞዝ ማሻሻያ ጥናት እየተዘጋጀ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። "የሰራተኞች የውስጥ ስራ ዕድገት በመመሪያና የተለያዩ አካላትን ባካተተ በኮሚቴ የሚሰራ በመሆኑ ምንም አይነት ዝምድናና አድሎ የለም፤ ሰራተኞች ያለ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አይሰሩም፤ በዚህ መልኩ ቅሬታ ያቀረበ ሰራተኛም የለም" በማለት አስተባብለዋል። በድርጅቱ የዋና ስፍራ ተጠቃሚዎች ዘንድ የህይወት አድን ባለሙያዎችን ለመለየት ችግር መኖሩን ሥራ አስኪያጁ አምነዋል። ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል። "በእኔ በኩልም ተከታትሎ በማስፈጸሙ በኩል ክፍተት አለ" ሲሉም ተናግረዋል። የድርጅቱ ሰራተኞች በነጻነት የመናገር መብት በተመለከተም ሰራተኞች በግልጽነትና ባለቤትነት ስሜት እንዲናገሩ ነው የሚፈለገው እንጂ ሰራተኞች በመናገራቸው የሚወሰድ እርምጃ የለም ነው ያሉት። ሆቴሉ ተወዳዳሪና አትራፊ በመሆን ሰራተኛውን እዲጠቀም ለማድረግ የሚያስችሉ የሥራ ማስፋፊያና ማሻሻያ ተግባራት እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል።