የራስ መኮንን አዳራሽን ለማደስ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የራስ መኮንን አዳራሽን ለማደስ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ የሚገኘውን የራስ መኮንን አዳራሽ ለማደስ ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ ስምምነት ተፈረመ። ስምምነቱ በጃፓን ኤምባሲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት መካከል ነው የተፈረመው። ስምምነቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል የኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ ሀሰን፣ በጃፓን በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኪ ማትሲንጋ ናቸው የፈረሙት። በስምምነቱ መሰረት አዳራሹ ከመታደሱም በላይ በአዳዲስ መሳሪያዎች የሚደራጅ ይሆናልም ነው የተባለው። የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያና ጃፓን ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ከጃፓን ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት አለው፤ ያሉት ዳይሬክተሩ በ2010 መጀመሪያ የኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በዩኒቨርሲቲው መጥተው በምን መልኩ ሊያግዙን እንደሚችሉ ሲጠይቁ አዳራሹ ጥገና እንደሚያስፈልገው በመንገራችን ዛሬ ይህ ስምምነት ሊደረግ ችሏል ብለዋል። እስካሁን ስራውን ህጋዊ የማድረግ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ገልፀው አሁን ግን አዳራሹን ለማደስ በይፋ ስምምነት መፈፀሙን ነው ያስረዱት። አዳራሹ መታደሱ ህንፃው ለትውልድ እንዲሸጋገር ከማድረግ በተጨማሪ በአዳራሹ ስር የሚገኘውን ሙዚየም የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር ለመጨመርና ጎብኚዎች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል እንደሚሆንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኪ ማትሲንጋ በበኩላቸው በኢምባሲው የተደረገው ድጋፍ የራስ መኮንን አዳራሽ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለማደስ የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል። ስምምነቱ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገንና በአዳዲስ መሳሪያዎች ክፍሉን ለማደራጀት የሚያስችል እንደሆነም ነው ያብራሩት። እድሳቱ አዳራሹ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲቆይ ከማድረጉ ባሻገር በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ላለው ግንኙነት ማሳያ የሚሆን ቅርስ ያደርገዋልም ብለዋል። ኢትዮጵያና ጃፓን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የተጀመረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።