የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ አራተኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በመቐለ ከተማ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ አራተኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በመቐለ ከተማ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሴቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ሚና እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ለማድረስ በሚቻልበት ጉዳይ የሚመክር መሆኑን አስታወቀ። ጉባዔው "የተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በመቐለ ከተማ ከታህሳስ 7 እስከ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል። የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሰዓዳ ዑስማን እንደገለጹት፤ ጉባዔው በአገሪቱ በተደረገው ለውጥ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና እያደገ ባለበት ወቅት መካሄዱ የተለየ ያደርገዋል። ጉባዔው የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር በሚወርድበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በኢህአዴግ ሴቶች ሊግ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ከሁለት ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል እንደሚደረግ የገለጹት ወይዘሮ ሰዓዳ ዘንድሮ ጉባዔውን ለማካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል። በጉባዔው በሦስት ቀን ቆይታው በሦስተኛው መደበኛ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመገምገም ጥንካሬን ማስፋት እንዲሁም ክፍተቶችን በማረም ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ተናግረዋል። በአገሪቱ ያለው ለውጥ እንዲቀጥል የሰላም ሚና ከፍተኛ በመሆኑ አባላቱ የሰላም አደናቃፊ ኃይሎችን በመታገልና ለውጡን በማስቀጠል ረገድ በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። በጉባዔው ቀጣይ ሊጉን የሚመሩ አመራሮች እንደሚመረጥም ወይዘሮ ሰዓዳ አመልክተዋል። በጉባዔው 700 አባላት ተሳታፊ ሲሆኑ 620ዎቹ በድምጽ የሚሳተፉ እንደሆኑ ያስረዱት ወይዘሮ ሰዓዳ ሴት ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከተለያዩ አደረጃጀቶች የሚሳተፉ ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙ ተናግረዋል። በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ ከአባላቱና ተጋባዥ እንግዶቹ በተጨማሪ ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ 500 ሴቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተበሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። ጉባዔው በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ለውጦችን ለማስቀጠልና በኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት የሚደረግበት ጉዳይ እንደሆነም ወይዘሮ ሰዓዳ ገልጸዋል።