ክፍለ ከተሞች ለአትሌቲክስ ስፖርት እድገት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ክፍለ ከተሞች ለአትሌቲክስ ስፖርት እድገት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2011 በመዲናዋ የሚገኙ ክፍለ ከተሞች ለአትሌቲክስ ስፖርት እድገት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል። ፌዴሬሽኑ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄዷል። በዚህ ጠቅላላ ጉባኤው የ2010 በጀት ዓመት የፌዴሬሽኑ የስራ ሪፖርት ፣ የ2010 የኦዲት ሪፖርት የ2011 ዓ.ም በጀት እቅድና የተሻሻሉ የፌዴሬሽኑ ደንቦችና መመሪያዎች ቀርበዋል። በጉባኤው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ወንዳለ ስጦታው ባለፈው ዓመት ከክፍለ ከተሞች ጋር ተቀራረቦ ለመስራት ብዙ ስራዎች ተሰርተው ነበር። ነገር ግን ለእግር ኳስ እንጂ ለአትሌክስ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን አንስተዋል። በቀጣይም ይህን በማስተካከል ክፍለ ከተሞች ከፌዴሬሽኑ ጋር በቅርበት ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለሰማዕት መርሃጥበብ አስተዳደሩ ለስፖርቱ ቅን አመለካከት እንዳለው ገልጸዋል። የከተማዋ ስፖርት ቢሮም ለአትሌቲክስም ሆነ ለሌሎች ስፖርቶች እድገት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ነው ያረጋገጡት። ፌዴሬሽኖችም ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ በኩል መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በትናንቱ ጉባኤ ላይ በ 2010 ዓ.ም በጀት ዓመት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ክለቦችና ተቋማት የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል። በዚህም መሰረት ባለፈው ዓመት የመከላከያ አትሌቲክስ ስፖርት ክለብ የተሻለ ውጤት በማስመዘገቡ ከብሄራዊ ፌዴሬሽኑ የ300 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን የ240 ሺህ ብርና የ180 ሺህ ብር እንደየቅደም ተከተላቸው ተሸላሚ ሆነዋል። ፌዴራል ማረሚያ ቤትና የፌዴራል ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ ደግሞ የ100 ሺህ እና 80 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። እንዲሁም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ጽህፈት ቤትም ለአትሌቲክስ ስፖርት ላበረከተው አስተዋጽኦ የ140 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ከብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ተበርክቶለታል። የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በረጅም ጊዜ የአትሌቲከስ ስፖርት አሰልጣኝነት ውጤታማ ለሆኑ አሰልጣኞችና ዳኞች እውቅና ሰጥቷል። በሌሎች ዘርፎችም በከተማ አትሌቲክስ ስፖርት የላቀ ስራ ሰርተዋል ላላቸው ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።