በመዲናዋ ካሉት መንገዶች የመብራት አገልግሎት ያላቸው ከ40 በመቶ አይበልጡም- መንገዶች ባለስልጣን

ህዳር 30/2011 በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት መንገዶች ውስጥ የመብራት አገልግሎት እያገኙ ያሉት ከ40 በመቶ  እንደማይበልጥ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል። ባለስልጣኑ እስከሚቀጥለው ዓመት  ዘጠና በመቶ የከተማዋ መንገዶች መብራት እንዲኖራቸው ከአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል። የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ሃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሰረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል፡፡ የመብራት ምሰሶዎች በየመንገዱ ቢተከልም ከሁለት ዓመት ወዲህ አብዛኛዎቹ አገልገሎት እንደማይሰጡ የጠቀሱት የአፍንጮ በር ነዋሪ አወል አማን ማታ ማታ ወደ መስጊድ ሲሄዱና ከስራ አምሽቶ ወደ ቤት ለመግባት ስጋት ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡ ምሰሶዎችና አምፖሎች ተሰባብረው እንደሚገኙ ያነሱት ነዋሪው አገልግሎት የማይሰጡ መብራቶች እንዲጠገኑ ጠይቀዋል። የጉለሌ አካባቢ ነዋሪ አቶ ፀጋዬ መኩሪያ አሽከርካሪ ናቸው፤ መንገዶች ማታ ማታ መብራት ከሌላቸው ለአሽከርካሪዎች ፈታኝ በመሆኑ የትራፊክ አደጋ ይከሰታል ብለዋል። አቶ ጸጋዬ እንደሚሉት ጉለሌ አካባቢ በርካታ መኪናዎችና እግረኞች የሚተላለፉበት ቢሆንም መብራት የላቸውም፤ ብዙዎችም አደጋ እየደረሰባቸው ነው፡፡ የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ ማቲዮስ ታምር ስራው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲዘዋወር ስለሚያደርገው በርካታ መንገዶችን እንዳየና መብራት እንደሌላቸው ነግሮናል። ውስጥ ለውስጥና በዋና መንገዶች መብራት በብዛት አለመኖሩ መሪን ያለ አግባብ የመጠቀም እድል ስለሚኖር የመጋጨት አጋጣሚውም ሰፊ ነው ብሏል። ከስድስት ኪሎ ሽሮ ሜዳ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ እንጦጦ፣ ከእንቁላል ፋብሪካ ዊንጌት ባሉ መንገዶች  እንደሚሰሩ የገለፁት  በአዲስ አበባ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ቁጥጥር አባል ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው በለጠ  ከነዚህ መንገዶችም  አብዛኛዎቹ  መብራት የላቸው ብለዋል፡፡ መዲናዋ በተሽከርካሪዎችና በእግረኞች የተጨናነቀች በመሆኗ በጨለማ ወቅት መብራት አለመኖሩ የትራፊክ አደጋን አባብሷል ነው ያሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ። መብራት ከሌለ አሽከርካሪዎች ረጅም መብራት የመጠቀም እድላቸው ሰፊ ነው ያሉት ረዳት ኢንስፔክተር መራጭ ድንጌቻ፤ ከፊት ለፊት የሚመጡ መኪናዎችን እይታ ሙሉ ለሙሉ  በመሸፈን ለአደጋ ያጋልጣል ብለዋል። “ከእንቁላል ፋብርካ እስከ ዊንጌት ብዙ ሆስፒታሎች ስላሉ ህሙማንን የያዙ ተሽከርካሪዎች ቀንና ሌሊት ይመላለሳሉ፤ ባለፈው ዓመት በዚያ መንገድ በርካታ ሰዎች ተገጭተዋል” ነው ያሉት። ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው “ከዚህ ቀደም በአዲሱ ገበያ ዊንጌት በሚወስደው መንገድ አንዲት ሰው ተገጭታ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ሌሊቱን ሙሉ መኪና ሲመላለስባት አድሮ የገላዋ ዱቄት ነው የተነሳው” ሲሉ ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ክስተት ነግረውናል። በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብራት ክትትል ባለሙያ ኢንጅነር ደረጀ ሃይሉ የከተማዋ መንገዶች አንዳንዶቹ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸው ገልጸው “ከጉርድ ሾላ ኦቨር ፓስ፣ መገናኛ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ከስድስት ወር በፊት ተጠይቆ የዋጋ ግምት አልተመለሰልንም” ነው ያሉት። የቦሌ አራብሳ መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት ለአገልገሎት ክፍት ሆኖ የመብራት ምሰሶ ቢተከልም መብራት እንዳልተለቀቀ የገለጹት ኢንጅነር ደረጀ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ ኪዳነምህረት የምሰሶ ተከላና  የገመድ ዝርጋታ የማሟላት ስራ  ተከናውኖ  የሃይል ዋጋ ግምት እንዲላክለት ከአንድ ወር ወዲህ መጠየቁን ተናግረዋል። በባለስልጣኑ የድንገተኛና አንሰለሪ ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዘውዱ ባይህ በበኩላቸው መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩ 37 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የቀለበት መንገዶች ባለፈው ዓመት ተጠግነው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል። ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላት የመብራት ቁሳቁሶችን ከአገልግሎት ውጪ እያደረጉና እየዘረፉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘውዱ ከዮሴፍ-ቦሌ ሚካኤል፣ ከአየር መንገድ አደባባይ-ኢምፔሪያል፣ ሸጎሌ ከጎጃም በር-እስከ ዊንጌት እንዲሁም 18 ማዞሪያ፣ ከ3 ቁጥር ማዞሪያ-አለርት ቁሳቁሶቹ በየጊዜው እየጠፉ ተቸግረናል ነው ያሉት። የተበላሹትን ወደ አገልገሎት ለመመለስ በራስ ሃይልና በጨረታ እየተጠገኑ መሆኑን ያነሱት ቡድን መሪው አሮጌ መብራቶችን ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። በከተማዋ መንገዶች  ከ40 በመቶ የማይበልጡ የመብራት አገልግሎት ያላቸው ሲሆን  ባለሥልጣኑ 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ ጥገና እየሰራ ነው፤ በዚህ በጀት ዓመትም ሽፋኑን 90 በመቶ ለማድረስ   እየተሰራ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ በበኩላቸው መንገዶች ባለስልጣን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ባለው ውል መሰረት ቆጣሪና ትራንስፎርመር እየገጠምን ነው ብለዋል። ሆኖም የሲቪል ስራዎች በመንገዶች ባለስልጣን በኩል ባለመጠናቀቃቸውና የመንገድ ርክክብ ባለማድረጋቸው ምክንያት መብራት የማያገኙ መንገዶች መኖራቸውን ተናግረዋል። “የካ አባዶ አንድ መንገድ፣ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ መንገድ ተገምቷል፣ ቦሌ አራብሳ እየተገመተ ነው፣ ጎሮ ቱሉ ዲምቱ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ተገጥሟል፣ ከሲኤምሲ አደባባይ እስከ ካራ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ቢገጠምም መንገዱን ርክክብ አላደረጉም፣ ከዊንጌት አደባባይ እስከራስ ደስታ ሆስፒታል ላለው መንገዶች ባለስልጣን ግምት አላመጣም፣ ዓለም ባንክ ቤቴል አየር ጤና ፍርድ ቤት ያሉት ያልተጠናቀቁ የሲቪል ስራዎች ሲጠናቀቁ ሃይል ይለቀቅላቸዋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም