በውጭ አገራት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ድምጽ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት የቢቢኤን አመራሮች ኢትዮጵያ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ አገራት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ድምጽ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት የቢቢኤን አመራሮች ኢትዮጵያ ገቡ
አዲስ አበባ ህዳር 30/2011 በውጭ ሃገራት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ድምጽ ሆኖ ሲሰራ የቆየው ቢቢኤን (በረካ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ) የመገናኛ ብዙሃን መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ዛሬ ገብተዋል። የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የሙስሊም ማሀበረሰብ ክፍሎች ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል። የቢቢኤን ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሳዲቅ አህመድ እንደተናገሩት፤ ቢቢኤን ባለፉት ሰባት አመታት መሰረቱን በአሜሪካ በማድረግ የሙስሊም ማህበረሰብ ንቅናቄው መሪዎችን ድምጽ በማስተጋባትና ወጣቶች ወደ አላስፈላጊ ግጭቶች ውስጥ እንዳይገቡ ሲሰራ ቆይቷል። በውጭ አገሮች የሚገኙ የሀይማኖት መሪዎችና ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸውን የጋራ መድረኮችንም በማዘጋጀት አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። "ላለፉት ሰባት አመታት ወደ አገራችን መግባት አንችልም ነበር በአሁኑ ወቅት ግን በአገሪቱ በመጣው ለውጥ ወደ የምንወዳት አገራችን በመምጣታችን ልዩ ደስታ ተሰምቶናል" ሲሉም አቶ ሳዲቅ ተናግረዋል። በቀጣይም ለዳያስፖራው ማህበረሰብ ድልድይ በመሆን የአገሪቱ ሰላምና ዕድገት እንዲጠናክር ከባላድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በተለይም የሙስሊም ማህበረሰብ ያማከለና ማህበረሰቡ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችልበትን የመገናኛ ብዙሃን ተቋም አሰራር ለመዘርጋት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በቢቢኤን በጋዜጠኝነት ይሰሩ የነበሩት አቶ አብዱራህማን አህመድ በበኩላቸው የሙስሊሙ ማህበረሰብ አገር ወዳድና ጥያቄዎቹንም በሰላማዊ መንገድ ሲያነሳ የቆየ ቢሆንም ላለፉት አመታት ሲጨቆን እንደቆየ ተናግረዋል። ማህበረሰቡ በአሁኑ ወቅት ያገኘውን ነጻነት ተጠቅሞ ለአገሪቱም አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችልባቸው መንገዶች ላይና ኢትዮጵያውያንን በዘር በሀይማኖት ሳይከፋፈሉ አንድነታቸውን ለማጠናክር እንደሚሰሩ ነው የገለጹት። ሙስሊሙ ማህበረሰብ በአገር ግንባታ፣ በአገር አንድነትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከለውጡ ጎን በመሆን የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍና በሙያ ለማገዝ ወደ አገራቸው መግባታቸውን አስረድተዋል። በሙስሊሙ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስም በመጠቀም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ እንደሚሰሩም አንስተዋል። በአክሱም የሚገኙ የሙስሊሙ ማህበረሰብ በእምነት ነጻነታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ተቋማዊ የአደረጃጀት ስራዎችንም የመደገፍ ስራ እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል።