ከልደታ ፀበል እስከ ደንበል ያለው መንገድ ግንባታ ታህሳስ መጨረሻ ይጠናቀቃል

93
አዲስ አበባ  ህዳር 29/2011 ከልደታ ፀበል- በጋዘቦ አደባባይ- ደንበል የተጀመረው የስድስት ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በቀጣዩ ወር መጨረሻ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ የተጀመረው ከአራት ዓመታት በፊት ሲሆን ለአሰራር አመቺነት ሲባል በምዕራፍ ተከፍሎ ሲካሔድ እንደነበር ተገልጿል። ከዚህ መካከል ከልደታ ፀበል እስከ ቡልጋሪያ ፤ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እስከ ቦሌ ደንበል የሚደርሱት የማስፋፊያ ፕሮጀቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን  ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደ ገብርኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመገንባት ላይ ያለው ከልደታ ፀበል ጋዘቦ አደባባይ- ደንበል ድረስ ያለው ፕሮጀት በቀጣይ ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓም ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ። በ550 ሚሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ላይ ያለው ይሕው መንገድ የ30 ሜትር ስፋት እንዳለውም አመልክተዋል። ፕሮጀክቱ በ2010 ዓም ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በወሰን ማስከበር፣ በዲዛይን ለውጥና ለሚነሱ ሰዎች ተለዋጭ የመኖሪያ ቤት የመስጠት ስራ ጊዜ በመውሰዱ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማስኬድ አልተቻለም ብለዋል። የመንገድ ግንባታው መጠናቀቅ ለህብረተሰቡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጥኡማይ ህብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።  አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ስድስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም