ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ሳምንት ይጀመራል

አዲስ አበባ ህዳር 29/2011 10 ክለቦች የሚሳተፉበት የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል። ጎንደር ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዓመት አዲስ ተሳታፊ ክለብ እንደሆነም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ፌዴራል ፖሊስ ከመቐለ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ 30 ደቂቃ ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከመከላከያ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ ይጨዋታሉ። ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ አዲስ ተሳታፊ ጎንደር ከተማ እንዲሁም ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ህዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የባለፈው በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ መስራት እንዳለባቸው የጉባኤው አባላት መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶችን ለማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑንና ፌዴሬሽኑም በዚህ የውድድር ዓመት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጿል። የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛው የውድድር ዓመቱ ነው። ፕሪሚየር ሊጉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን መከላከያ በ20009 ዓ.ም እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ  የባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም