ከዚህ ዓመት ጀምሮ የመንግስት ተቋማት በዘመናዊ መንገድ ግዥ ይፈጽማሉ

100
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ የመንግስት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በመጠቀም ግዥ እንደሚፈጽሙ የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታወቀ። የግዥ ስርዓቱን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በመጠቀም ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከዓለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ አማካሪዎችን ቀጥሮ ሲሰራ መቆየቱ ተነግሯል። የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ የተመረጡ የመንግስት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ዘዴን በመጠቀም ግዥ ይፈጽማሉ። በተለይ መንግስት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ግዥ የሚፈጽምላቸው ተቋማት ላይ ይህን ዘዴ ለመጠቀም ቅድመ-ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት። አገልግሎቱ አሁን እየሰራበት ያለውን የግዥ ሂደት በማዘመን፣ ቀልጣፋና ግልጽ አሰራር ለመከተል ኤሌክትሮኒክስ ዘዴው ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል። በዘንድሮው ዓመት በሙከራ ደረጃ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ከሚፈጽሙ ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ እንዲሁም የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ይገኙበታል። ኤሌክትሮኒክስ ዘዴው በተመረጡ ተቋማት ዘንድሮ ይጀመር እንጂ ውጤታማነቱ ታይቶ በሌሎቹም ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። የዕቃ አቅራቢዎች እጥረት፣ የስልክና የኢንተርኔት መቆራረጥ በትግበራ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም አንስተዋል።  የኤሌክትሮኒክስ ግዥው ከሰው ንክኪ የጸዳ ሲሆን በግዥ ሂደት ያሉ መጓተቶችንና ቅሬታዎችን ያስቀራል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም