የጅቡቲው ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞን ሸኙ - ኢዜአ አማርኛ
የጅቡቲው ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞን ሸኙ
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞን ሸኙ። ፕሬዚዳንቱ በጅቡቲ ለሶስት ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩትን አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞን ትናንት መሸኘታቸው ነው የተገለጸው። ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በሽኝቱ ላይ አምባሳደር ሻሜቦ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ለተመዘገቡ ድሎች ዓይነተኛ ሚና በመጫወታቸው አመስግነዋቸዋል፡፡ አክለውም መንግስታቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ ነው ያረጋገጡት። አምባሳደር ሻሜቦ በበኩላቸው በጅቡቲ ቆይታቸው ከጎናቸው በመሆንና ጥያቄዎችን በፍጥነት በመመለስ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ እገዛ ላደረጉት ለፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በነበራቸው የስራ ዘመን ግልጽና ቅን ለሆነው የጅቡቲ ህዝብ አምባሳደሩ አድናቆታቸውን ችረዋል። ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለችም ሲሉ ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነም በጅቡቲ የስራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ለተሸኙት አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ በተደረገው ፕሮግራም በእንግድነት ተጋብዘው እንደነበር ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ የተላከው መረጃ ያመለክታል።