ቀጥታ፡

ብዙዎቹ የአዲስ አበባ ታሪካዊ ቅርሶች በችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅርሶችና ታሪካዊ ህንፃዎች ከሚከኙበት ችግር ለመታደግ ባለሃብቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው የመዲናዋ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ። ቢሮው የከተማዋን ሁኔታ፣ አኗኗርና ነባር ሰፈሮች በመልሶ ማልማት ሥራ ታሪካቸው እንዳይረሳ በተለያዩ ዘዴዎች ሰንዶ የማስቀመጥ ሥራ እየሰራ እንደሆነም አስታውቋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ቁጥጥርና ምዝገባ ቡድን መሪ  አቶ ደረጄ ስዩም እንደገለጹት በመዲናዋ ከ440 በላይ ታሪካዊ ህንፃዎች፣ ድልድዮች፣ ዋሻዎች፣ ሃውልቶችና ታሪካዊ ቦታዎች በቅርስነት ተመዝግበው ይገኛሉ። እስካሁን የአራት ኪሎ የድል ሃውልት፣ የስድስት ኪሎ የሰማዕታት ሃውልት፣ የአጼ ሚኒልክ ሃውልት፣ የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልትና ሴባስቶፖል ቅርሶችን ጥናት በማድረግ የእድሳት ሥራ ተሰርቷል። ነገር ግን ጥንታዊውን የዋሻ ሚካኤልን ጨምሮ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቅርሶች በችግር ውስጥ የሚገኙና አፋጣኝ እድሳት የሚፈልጉ መሆናቸውን አልሸሸጉም። ቢሮው አቅሙ በቻለው መልኩ እድሳትና ጥገና ቢያደርግም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መሆናቸውና በታሪካዊ ቤቶቹ ውስጥ ነዋሪዎች መኖራቸው ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ መጥቷል ሲሉም ተናግረዋል። በታሪካዊ ቦታና ሰፈሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ተለዋጭ ቤት ተሰጥቶ ቤቶችን ለማደስ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመው፤ በአዲስ አበባ የሚገኙትን ቅርስና ታሪካዊ ህንፃዎች ለማደስና ለመጠገን ባለሃብቶችና ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል። ቢሮው የከተማዋን ነባር ሰፈሮች በመልሶ ማልማት ሥራ ታሪካቸው እንዳይረሳ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀምም በሰነድ የማስቀመጥ ሥራ እየሰራ እንደሆነም አቶ ደረጄ ገልጸዋል። ቦታዎቹን በዲጂታል መሳሪያ ሰንዶ ከመያዝና ከማስቀመጥ ባለፈ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲያውቋቸው በመጽሔት፣ በብሮሸርና በመዲናዋ ለቱሪስት መዳረሻ ተብለው በተለያዩ ቦታዎች ላይ የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉም አክለዋል። በተለይ የከተማ ቅርሶችና ታሪካዊ ቦታዎች ለቱሪስት ክፍት እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። አዲስ አበባ ከመቆርቆሯ በፊት የነበራት ገጽታና ከተቆረቆረች በኋላ ያሏት ቅርሶች መኖራቸው ከቢሮው የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም