የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚደረጉ ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል። 12 ክለቦችን በሚያሳትፈው ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ-ግብር ትናንት በተደረገ አንድ ጨዋታ ተጀምሯል። ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጥረት ኮርፖሬት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈ ሲሆን የዛሬው ጨዋታ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ ነው። ጥረት ኮርፖሬት እስካሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በአንዱ ሲያሸንፍ በሌላኛው ሽንፈት ገጥሞታል። ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ስምንት ሰዓት አዲስ አበባ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። አዲስ አበባ ከተማ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፈ ሲሆን ከአዳማ ከተማ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ አሸንፎ አንድ አቻ ወጥቷል። በክልል በድሬዳዋ ስታዲየም በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጫወታሉ። አርባ ምንጭ ከተማ እስካሁን በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ አሸንፎ አንድ ተሸንፏል። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ኢትዮ-ኤሌትሪክ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል። ሁለቱ ክለቦች እስካሁን ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፉ ሲሆን ጨዋታው ሁለቱ ክለቦች በሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው። በዲላ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጌዲኦ ዲላ የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናግዳል። ሁለቱም ክለቦች ያደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፉ ሲሆን የሚያደርጉት ጨዋታ ቡድኖቹ የማሸነፍ ጉዟቸውን ለማስቀጠል በመሆኑ በሳምንቱ ከሚደርጉት ጨዋታዎች ትኩረትን ያገኘ ነው። ትናንት በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሃዋሳ ስታዲየም በተደረገ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ መከላከያን አስተናግዶ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ጌዲኦ ዲላና መከላከያ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 11ኛ እና 12ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጎን ኮከብ አግቢነት ረሂማ ዘርጋው በሶስት ግብ እየመራች ሲሆን፣ የድሬዳዋ ከተማዋ አይዳ ዑስማን የአዲስ አበባ ከተማዎቹ ፎዚያ መሐመድና ፍቅርተ ብርሃኑና የሀዋሳ ከተማዋ ምርቃት ፈለቀ በተመሳሳይ ሁለት ግቦች ይከተላሉ። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።