ቀጥታ፡

አትሌት ኦብስኔ ዳባ ለአራት ዓመት ከውድድር ታገደች

አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 አትሌት ኦብስኔ ዳባ ለአራት ዓመት በማንኛውም የሩጫ ውድድሮች እንዳትካፈል እገዳ ተላለፈባት። አትሌቷ ላይ እገዳው የተላለፈው የአበረታች መድኃኒት ወስዳ በመገኘቷ ነው። አትሌቷ አበረታች መድኃኒቱን የወሰደቸው ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር በቻይና ሀገር በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ሲሆን በቻይና ሀገር የጸረ አበረታች መድሀኒት ቅመሞች ጽህፈት ቤት በተደረገላት ምርመራ አበረታች መድኃኒት መውሰዷ ነው የተነገረው። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ቁጥጥር ጽህፈት ቤት አትሌቷ ለአራት ዓመት ከማንኛውም የሩጫ ውድድሮች እንድትታገድ ወስኖባታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም አትሌቶቻችን በአቋራጭ ለማሸነፍ የሚያደርጉት ሙከራ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል። ፌዴሬሽኑ የብሄራዊ የጸረ አበረታች መድኃኒት ቅመሞች ውሳኔ እንደሚደግፍና አትሌቶች በተፈጥሯዊ መልኩ ብቻ ልምምዳቸውን በመስራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በመገንዘብ ወደ አልተገባ ነገር እንዳይገቡ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም