ቀጥታ፡

የመከላከያ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ጨዋታ ወደ ሰኞ ተላለፈ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 በ13ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት መከላከያ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ነገ ሊያደርጉት የነበረው የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ወደ ሰኞ ተሸጋግሯል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው ጨዋታው ወደ ሰኞ የተላለፈው 13ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚከበር በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል። የመቐለ ሰብአ እንደርታና ባህርዳር ከተማ ከነገ በስቲያ ሊያደርጉት የነበረው የአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙም ይታወቃል። ለዚህም ምክንያት የሆነው የትግራይና የአማራ ክልል እግር ኳስ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ እንደማይካሄዱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መግለጹ ነው። እሁድ የሚደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ግን በተያዘለት መርሀ ግብር መሠረት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ገና ከጅምሩ በተለያዩ ምክንያቶች በመርሃ ግብር መቀያየርና መቆራረጥ ወጥነት በሌለው መልኩ እየተካሄደ የሚገኘው የሊጉ ጨዋታ በየሳምንቱ የሊጉ ጨዋታዎች የመርሃ ግብር ማስተካካያ ማድረግ የተለመደ ነገር ሆኗል። ዛሬ በኢትዮጵያ አንደኛ ዲቪዚዮን ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሊካሄድ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጥረት ኮርፖሬት ጨዋታ በስታዲየሙ ባለው የበዓል ቅድመ ዝግጅት ቦሌ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ከቀኑ 10 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ነገ በኢትዮጵያ አንደኛ ዲቪዚዮን ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም አዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በበዓሉ ምክንያት ሰኞ ታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይካሄዳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም