ቀጥታ፡

ነገ የሚከበረውን 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ምክንያት በማድረግ የጎዳና ላይ የባህል ትርኢት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 በአዲስ አበባ ነገ የሚከበረውን 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀን ምክንያት በማድረግ የብሔሮቹ ተወካዮች የጎዳና ላይ የባህልትርኢት(ካርኒቫል) እየተካሄደ ነው። ትርኢቱ መነሻውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር(ማዘጋጃ ቤት) አድርጎ መድረሻው መስቀል አደባባይ ይሆናል። በትርኢቱ ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የመጡ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጭፈራና አለባበስ ባህል እያሳዩ ይገኛሉ። የትርኢቱ ዋና ዓላማ  የብሔሮችን ጭፈራና አለባበስ እርስ በእርስ ለማስተዋወቅና ኢትዮጵያ ውብ ባህል ያላት አገር መሆኗን ለማጉላት ነው። መርሃ ግብሩም የዋዜማ ምሽት በብሔራዊ ትያትር የሚኖረው ሲሆን በዚያም ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይቀርባሉ። ለአስራ ሶስተኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን እያስተናገደች የምትገኘው አዲስ አበባ ቀኑን በማስመልከት ከሰሞኑ ያዘጋጀችው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን ከሰሞኑ እያቀረበች ትገኛለች። ነገ በደማቅ ሁኔታ በሚጠቃለለው በዚሁ በዓል ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችንም በአምስቱም በሮቿ እየተቀበለች ትገኛለች። በፓናል ውይይት፣ በአውደ ርዕይ፣ በሙዚቃ ድግስ፣ በቡና ጠጡና ሌሎችም ዝግጅቶች ሲከበር የነበረው በዓልም ነገ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ማጠቃለያውን ያገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም