የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ስርዓት ገጽታዎች በፖለቲካ ባለሙያዎች እይታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ስርዓት ገጽታዎች በፖለቲካ ባለሙያዎች እይታ
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው የፌዴራሊዝም ስርዓት አሁንም የተለያዩ አካላትን ያነጋግራል። ስርዓቱ ብሔርን መሰረት ያደረገ ነው በሚል የክርክር ሃሳብ መሆኑም ቀጥሏል። አንዳንዶች የፌዴራሊዝም ስርዓቱ አሁን በኢትዮጵያ ላለው ችግር መንስኤ መሆኑን፤ ብሔርተኝነት ላይ የሚያተኩርና የዜግነት ጉዳይን የሚያሳንስ ነው ሲሉ ይገልጻሉ። በተቃራኒው 'ተጨቁነው የነበሩ ብሔሮች እንዲከበሩ አግዟል' የሚል መከራከሪያ ሃሳብም ይነሳል። የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ አሁን በኢትዮጵያ ያለው የአስተዳደር ስርዓት ግጭትን ጨምሮ አሁን ለገጠሟት ችግሮች መንስኤ ነው በማለት ይናገራሉ። "የመንግስት አወቃቀሩ የተወሰኑ ብሔሮች ላይ መሰረት ያደረገው የገዥው ፓርቲ አደረጃጀት ኢትዮጵያ በብሔር ጉዳይ ላይ እንድትሽከረከር እያደረጋት ነው" የሚል የክርርክር ሀሳብ ያነሳሉ። "በኢትዮጵያ አሁን ላለው የቀውሱ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንደኛው ብሔር ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ መዋቅር ነው እኛ በዓለም ደረጃ ኢትዮጵያን ብቸኛ የሚያደርጋት ህገ-መንግስቱ እኛ ብሔር ብሔረሰቦች በሌላ ቋንቋ እኛ ህዝቦች ሳይሆን ጎሳዎች በሚል ከአገራዊ አንድነት ብሔረተኝነትን የሚያጎላ ነው።" ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ተኮር ግጭቶች ተስተናግደዋል፤ በዚህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። እንደ ኦባንግ ሜቶ ገለጻ ግጭቶቹ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችው "የብሔር ተኮር የፖለቲካ መዋቅር ውጤት ነው"። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ተንታኝና መምህር ዶክተር ሳሙኤል ነጋሽ እንደሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት እየታዩ ላሉት ችግሮች መንስኤ አይደለም። ስርዓቱ ከችግር ይልቅ "ለረዥም ጊዜ የቆየውን የብሔሮች ጭቆናና ለእኩልነት ማጣት ምላሽ የሰጠ ነው" ሲሉ ያምናሉ የፖለቲካ ተንታኙ። " በኢትዮጵያ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጭቆና እንደ ቀላል ነገር የሚታይ አይደለም አገሪቷ ውሰጥ ብዙ ብሔሮች አሉ በቀደሙት መንግስታት ጭቆናና መገለል ደርሶባቸዋል። የነበረው ነገር የብሔር ብሔርተኞች ፍትህና እኩልነት አለመኖርን አስወግደው የፌደራል ስርአት ለመገንባት የእውነት ጦርነት ትግል እንዲያደርጉ ዋንኛ ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ።" ስርዓቱ የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታ በድጋሚ በማዋቀርና በብሔሮች መካከል እኩልነት እንዲኖር በማድረግ የፖለቲካ ተሳትፏቸው እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል። ዶክተር ሳሙኤል በብሔሮች መካከል እየጨመረ የመጣውን ውጥረትና ግጭት እንደሚገነዘቡና የዚህም ችግር ዋንኛ መንስኤ "የፌዴራል ስርዓቱን በአግባቡ ካለመተግበር የመጣ ነው" ይላሉ። "በመሰረታዊነት የፌዴራሊዝም ስርዓት ለኢትዮጵያ አዲስ ክስተት ነው ስርአቱ በራሱ አንዳንዳድ ችግሮች ሊያመጣ ይቻላል ያም ቢሆን በግሌ ብሔርና ቋንቋ ላይ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ተግባር በኢትዮጵያ ላሉ ችግሮች መንስኤ ነው ብዬ አላምንም።” ሁለቱ አስተያየት ሰጪዎች የፌዴራሊዝም ስርዓት ባለው ተጽእኖ ላይ የተለያየ ምልከታ ቢኖራቸውም አሁን በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ ስራዎች አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲና መረጋጋት እንደሚመራት ተስፋ አድርገዋል። የፖለቲካና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ አሁን ያለው ለውጥ ጥሩ ነገር ይዞ እንደሚመጣና ዜጋ ተኮር አመለካከት እንዲኖር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። ያም ቢሆን ገዥው ፓርቲ በለውጡ ውስጥ መሄድ አለበት ብለው ፓርቲው አሁን ባለበት አደረጃጀት ችግሮችን ለመፍታት እንደማይችል ገልጸዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሁን ኢህአዴግን እየመሩ ነው ፓርቲው መሰረት ያደረገው ብሔር ላይ ነው አሁን ባለው ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርቲው ላይ የለውጥ ስራ መስራት አለባቸው” የፖለቲካ ተንታኙና መምህሩ ዶክተር ሳሙኤል በኢትዮጵያ እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲኖርና በዚህም የፌዴራል ስርዓቱ ዘላቂነት እንዲኖረው በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል። በዚህ ረገድ አሁን ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው ለውጥ ይሄን ነገር ደረጃ በደረጃ እንድታሳካ እንደሚያደርጋት ነው የሚገልጹት። "አሁን ያለውን የለውጥ ሁኔታ ስናይ በተለያዩ አካላት መካከል ማለትም ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ዳያስፖራና ሌሎች ይበልጥ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በአገራችው ጉዳይ ላይ እንዲያወያዩ አድርጓል። ይሄ ጉልህ ለውጥ ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ በሀሳብ ላይ የተመሰረቱ ብዙ ምርጫዎች እንዲኖሩት ይረዳል።" ኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት ቋንቋና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ የፌዴራሊዝም ስርዓት እየተገበረች ትገኛለች።