'የፌዴሬሽኑ አሰራር ግልጽነት የጎደለው ነው' - የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት - ኢዜአ አማርኛ
'የፌዴሬሽኑ አሰራር ግልጽነት የጎደለው ነው' - የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰራርና ውሳኔዎች ላይ እምነት እንደሌላቸው የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት ተናገሩ። ፌዴሬሽኑ ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በእግር ኳሱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከስፖርት ጋዜጠኞችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ የአንድ ቀን የምክክር መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ ላይ የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ አማረ ያለው 'የፌዴሬሽኑ አሰራር ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ እምነት የሚጣልበት አይደለም' ብለዋል። በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች የሚያሳልፉት ውሳኔም ወገንተኝነት የሚታይበት እንደሆነ ተናግረዋል። በክለቦችና ተጫዋች ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተዓማኒነት የጎደላቸው በመሆናቸው ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት እየሆኑ በመሆኑ 'ፌዴሬሽኑ ራሱን ማየት አለበት' ሲሉም አመልክተዋል። የመድረኩ ተሳታፊ ጋዜጠኞችም በእግር ኳሱ ላይ የሚታየውን ስርዓት አልበኝነት ለማስወገድ ከሁሉም በላይ ክለቦችና ፌዴሬሽኑ ራሳቸውን መፈተሽ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ፌዴሬሽኑ ከጋዜጠኞች ጋር ተቀራርቦ በመስራት በኩል ሰፊ ክፍተት ያለበት በመሆኑ መረጃዎችን በወቅቱ 'ተደራሽ እያደረገ አይደለም' ብሏል። መረጃዎችን በወቅቱ የማያገኝ ጋዜጠኛ ደግሞ በእግር ኳስ ሜዳዎች ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን በተረዳበት ሁኔታ እንዲዘግብና ትንንሽ ጉዳዮችንም አጋኖ ማቅረብ እንደሚታይ ተናግሯል። ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ለማስተካከል ከሁሉም በላይ ፌዴሬሽኑና ክለቦች በጋራ መስራት አለባቸው ያለው ደግሞ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ክፍሌ ነው። በእግር ኳስ ሜዳዎች ላይ የሚከሰቱ ሁከትና ብጥብጦችን ለማስቀረት የክለብ ከደጋፊዎች የመፍትሄው ተዋናይ መሆን አለባቸውም ብሏል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም መረጃዎችን በፍጥነት ለጋዜጠኞች በመስጠት በኩል ችግሮች እንዳሉ በመግለጽ ይህንን መፍታት የሚያስችል አደረጃጀት 'የሚፈጠር ይሆናል' ሲሉ መልሰዋል። ከዚህ በፊት የፌዴሬሽኑ ገጽታ መበላሸቱን በመግለጽም ስምና ዝናውን ወደ ቀድሞው ለመመለስና እምነት የሚጣልበት ተቋም ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል። የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ እርስቱ ይርዳው በበኩላቸው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግሩን ለመፍታትም ለስፖርቱ ዕድገት የጋዜጠኞች ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይ ኮሚሽኑ ከስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጋር በቅርበት ለመስራትና ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነም አስታውቀዋል።