ቀጥታ፡

ሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 የ2011ዓ.ም ሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች  የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በዘንድሮው ዓመት በሊጉ ተሳታፊ የሆነው እንግዳው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከመከላከያ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ከጠዋቱ አራት ሰዓት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከሙገር ሲሚንቶ ጋር ይጫወታሉ። በክልል ከተሞች በባህርዳር ሚሊኒየም ሜዳ ጣና ባህርዳር ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ፣ ባሌ ሮቤ ላይ መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ፖሊስ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ጣና ባህርዳር፣ ሙገር ሲሚንቶና መከላከያ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸውን አሸንፈዋል። በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ሶዶ ላይ ወላይታ ዲቻ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባቀረበው ጥያቄ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል። በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ክለቦች ይሳተፋሉ። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽኑ ከ2005 ዓ.ም በሁለቱም ጾታዎች የፕሪሚየር ሊግ ውድድር እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በአሁኑ ሰዓት ያሉትን አራት ክለቦች ወደ ስድስት በመጨመር ውድድሩን በጥር ወር 2011 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ለመጀመር እቅድ ይዟል። ወላይታ ድቻና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በቅደም ተከተል የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግና የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም