እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ ዓመት የካርበን ልቀት የጨመረበት ነው - ሪፖርት

71
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 እየተጠናቀቀ ያለው የፈረንጆቹ 2018 በዓለም ላይ ከሌላው ጊዜ በተለየ የካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀት የጨመረበት መሆኑ ተነገረ። የቻይና ዜና አገልግሎት /ዥንዋ/ ዓለም አቀፍ የካርበን ፕሮጀክትን መረጃ ጠቅሶ እንደጻፈው በ2018 ለሙቀት መጨመር አንዱ ምክንያት የሆነው የካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀት ከ2 ነጥብ 7 በመቶ ወደ 37 ነጥብ 1 ቢሊዮን ቶን ከፍ ብሏል። ሪፖርቱ በመንገዶች ላይ የተሽከርካሪዎች ቁጥር መጨመርና በዓለም ላይ ጥቅም ላይ የሚውለው ከሰል ማሻቀብ ለካርበን ልቀት መጨመር በዋነኛነት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብሏል። የዓለም አቀፍ ካርበን ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር ፒፕ ካናዴል የነዳጅ ካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀት ቀደም ሲል ወደነበረበት መጠን መምጣቱ 'የሚያሳዝን ነው' ሲሉ ተደምጠዋል። የ2018 የዓለም ጠንካራ ልቀት በቀጣዩ 2019 የሚኖረውን የኢኮኖሚ እድገት ተከትሎ ሊቀጥል እንደሚችልም ትንበያቸውን አስቀምጠዋል። የአውስትራሊያ የልቀት መጠን ለተከታታይ አራት ዓመታት መጨመሩንም ሪፖርቱ አመላክቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ጥቅምት ባሰራጨው መረጃ አውስትራሊያ በ2030 የካርበን ልቀት መጠንን በ26 በመቶ ለመቀነስ ፓሪስ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ለማሳካት ትክክለኛው መስመር ላይ አለመሆኗን አስጠንቅቆ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል። ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የመጥፋት መስመር ውስጥ ገብታ እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ የልቀት መጠኑ በ2020 ሊብስ እንደሚችልም ጠቁሟል። የዓለም አቀፍ ካርበን ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር ፒፕ ካናዴል በሪፖርቱ የተካተተው መረጃ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ መስራት የምንፈልገውና እየሰራን ባለነው መካከል ያለውን ልዩነት ያሳያል በማለት ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም